የካቲት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ካለፈው በተሻለ መልኩ 8 ነጥብ 4 ሆኖ ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተጠናቀቀው 2016 ዓ.ም 8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ መግለጻቸው ይታወሳል።
ይህም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ጥቂት ሀገራት ተርታ ያሠለፈና በርካታ ሀገራትም ዕውቅና የሰጡት እንደሆነ ገልጸው ነበር።
በዘንድሮው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ካለፈው በተሻለ መልኩ 8 ነጥብ 4 ሆኖ እንደሚመዘገብ የገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል።
ይህ የተገለጸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት(ተመድ) የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘውን አዲሱ የአፍሪካ ማዕከል ርክክብ በተደረገበት ወቅት የገንዘብ ሚኒስቴር አህመድ ሽዴ ባደረጉት ንግግር ነው።
ይህንንም ለማሳካት በዘላቂ የፋይናንስ ሞዴል፣ የሀገር ውስጥ ተቋማት እንዲሁም መንግሥት የኢንቨስትመንት አካል እንዲሆን ለማስቻል እየተሰራ ነዉ ብለዋል።
በዋና ዋና ዘርፍ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በፋይናንስ ዘርፍ አገልግሎትና ምርታማነትን ለማጎልበት የግሉ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
የፋይናንስ ዘርፉን ማረጋጋት አንዱ ባለፉት ዓመታት የተሰራ ሥራ መሆኑን አንስተው፤ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ላይ የራሱን ሚና የሚጫወትበት ዕድል መመቻቸቱን ጠቁመዋል።
"ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሁሉን አቀፍ ሪፎርም አድርጋለች" ያሉት ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ ቀጣይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ በሚያስችል ቁመና ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ግቡን ለማሳካት የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢንዱትሪው የኤክስፖርት ድርሻ እንደ ሀገር እያደገ መሆኑንም የጠቆሙ ሲሆን፤ "አሁን ላይ 4 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት እንጠብቃለን" ብለዋል።
"በ2016 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 1 በመቶ ነጥብ ያደገ ሲሆን፤ በዚህ በተያዘው ዓመት 8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንጠብቃለን" ሲሉም ገልጸዋል።
እንደ አይ.ኤም.ኤፍ ትንበያ በፈረንጆቹ 2025 ኢትዮጵያ 6 ነጥብ 5 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ታስመዘግባለች ማለቱ ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በተያዘው ዓመት 8 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ
