የካቲት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የሚመረቱ የቀለም ምርት ጥራትን በሚመለከት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2015 ዓ.ም ጸድቆ በፈረንጆቹ በ2024 ተሻሽሎ የጸደቀው አዋጅ፤ ከሰኔ 1 ቀን 2017 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታዉቋል።
በጸደቀው አዋጅ በኢትዮጵያ የቀለም ኢንዱስትሪዎች የሚመረቱ የቀለም ምርቶች ከሊድ ነጻ እንዲሆኑ እንዲሁም የሊድ መጠናቸዉ ከፍተኛ የሆኑ እና መሰል ኬሚካሎች እንዳይመረቱ እና ወደ ገበያዉ እንዳይገቡ አስገዳጅ ክልከላ የሚያደርግ ሲሆን፤ እንዚህም ኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ መሆናቸው ተገልጿል።
ከአራት ወራት በኋላ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው ይህ አዋጅ የቀለም አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ እና ግንዛቤው እንዲኖራቸዉ እየተደረገ መሆኑን በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የገበያ እና ፋብሪካ ምርቶች ጥራት ማረጋገጥ ኃላፊ ተከተል ቢተው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት ከሰኔ 1 ጀምሮ አዋጁን ተግባራዊ በማያደርጉ ወይም በሕግ አግባብ በማያመርቱ አምራች ድርጅቶች ላይ እርምጃ እና ቅጣት እንደሚወሰድ አስረድተዋል።
ኃላፊዉ አክለውም አወጁን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እና የቁጥጥር ሥራዉን ለመጀመር በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኩል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በአዋጅ የጸደቀው ክልከላ በቀለም አምራች ኢንዱስትሪዎች ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑ በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የቀለም ምርት ጥራትን በሚመለከት የጸደቀው አዋጅ ከሰኔ ወር ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ይደረጋል ተባለ
