የካቲት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአሶሳ ከተማ አስተዳደር 'ሪቮ' መኪናው በታጣቂዎች ሊቃጠል እንደሆነ በመግለፅ፤ ባለንብረቱን አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ያታለሉ ወንድማማቾች በእስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

ተከሳሾች 1ኛ ያዕቆብ ያህያ እና 2ኛ ተከሳሽ መርቀኒ ያህያ የተባሉ ወንድማማቾች ሲሆኑ፤ ንብረትነቱ የግል ተበዳይ በሽር ኢትኔን የሆነው "ሪቮ" ተሽከርካሪ ለጥገና ወደ አዲስ አበባ ይዞ እንዲሄድ 1ኛ ተከሳሽ ተሰጥቶታል።

በመቀጠልም ተከሳሹ መኪናውን አስጠግኖ ከጨረሰ በኃላ ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ እያሽከረከረ እያለ፤ ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ ወረዳ ቤንጓ አካባቢ በታጣቂዎች ሳይታገት መታገቱን ለባለሃብቱ ያስታውቃል።

በተጨማሪም 'መኪናው ሊቃጠል በመሆኑ ማስለቀቂያ አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ተጠይቄያለሁ' በማለት ባለቤቱን አሳመነ በኋላ ገንዘቡን 2ኛ ተከሳሽ ወንድሙ የተቀበሉ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት ከባድ የማታለል ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

በዚህም ፖሊስ ሁለቱን ተከሳሾች በቁጥጥር ሥር አውሎ በሰውና ሰነድ ማስረጃ አስደግፎ ያጣራውን የምርመራ መዝገብ መላኩን የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር አወድ ሙስጠፋ ለአሐዱ ተናግረዋል።

የምርመራ መዝገቡ የደረሰው የአሶሳ ከተማ ፍትህ መምሪያ በፈጸሙት ከባድ የማታለል ወንጀል የመሰረተውን ክስ ለአሶሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልኳል። በዚህም ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን መዝገብ ከተመለከተ በኋላ ተከሳሾችን ጥፋተኛ ሲል ብይን ሰጥቷል።

ስለሆነም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችን እና ሌሎችንም ያስተምራል በማለት 1ኛ ተከሳሽ ያዕቆብ ያህያ በ4 ዓመት ፅኑ እስራት እና 15 ሺህ ብር እንዲቀጣ ውሳኔ ተላልፎበታል።

2ኛ ተከሳሽ መርቀኒ ያህያ ደግሞ በ4 ዓመት ፅኑ እስራት እና ሰባት ሺሕ ብር እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ