ጥር 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መደበኛውን የግብር መክፈያ ጊዜ ቀነ ገደብ ያሳለፉ ግብር ከፋዮች ክፍያቸውን በጊዜው ያልፈጸሙበትን ምክንያት በማቅረብ ተጨማሪ የመክፈያ ቀን ተራዝሞላቸው የሚጠበቅባቸውን የገቢ ግብር እየከፈሉ መሆኑን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ፤ "የግብር መክፈያው ቀነ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚመጡ ግብር ከፋዮች ‹‹በፍሬ ግብሩ ላይ ቅጣትን እና ተጨማሪ ወለድን ጨምረው ይከፍላሉ" ያሉ ሲሆን፤ ግብር ከፋዩ በወቅቱ ያልከፈለበትን በቂ ምክንያት ካቀረበ የሚከፍልበትን ጊዜ በማሳወቅ ቀነ ገደቡ እንዲራዘምለት ከተቋሙ ጋር ስምምነት መፈጸም እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ግብር ለመክፈል ፈቃደኛ ባለመሆን ግብር የሚሰውሩ ተቋማት እንዳሉ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ግዴታቸውን በማይወጡ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ላይ በአዋጁ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት የባንክ ሂሳባቸውን እስከ ማገድ የደረሰ ቅጣት እንደሚከተላቸው አስታውሰዋል፡፡
ግብር ከፋዮች ለተመሳሳይ ቅጣት እንዳይዳረጉ የሚጠበቅባቸውን የገቢ ግብር በወቅቱ እንዲከፍሉም አሳስበዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በተጨባጭ ምክንያት የግብር መክፈያ ጊዜ ላሳለፉ ግብር ከፋዮች ቀነ ገደቡ የሚራዘምበት አሰራር መኖሩ ተገለጸ
