የካቲት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክ ለመቀየር የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል።
መመሪያው ደረጃውን ጠብቆ ከመቀየር አንፃር ወሳኝ አሰራሮችን የያዘ ሲሆን፤ ከዚህም ባሻገር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችም ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ማሟላት ያለባቸውን ደረጃ የሚወስን ደረጃን ያካተተ መሆኑን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የትራንስፖርት አገልግሎትና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አሰፋ ሀዲስ ለአሐዱ ገልጸዋል።
በቅርቡም በባለሙያዎች እይታና በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማረጋገጫ ከተሰጠው በኋላ መመሪያው ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ42 ሺሕ በላይ ምዝገባ ያጠናቀቁ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንደሚገኙ የትራንስፖርት አገልግሎትና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪው ተናግረዋል።
ወደ 100 ሺሕ የሚጠጉ ደግሞ ያልተመዘገቡ ወይም ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ነገር ግን ሥራ ላይ ያልዋሉ ተሽከርካሪዎች እንደሚገኙ አክለው ገልጸዋል።
በተለይም የነዳጅ ተሽከርካሪ አውቶሞቢሎች መግባት ካቆሙ ከ2016 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በብዛት ወደ ሀገር ውስጥ መግባት መቻላቸውን በማንሳት፤ ከዛን በፊት የነበሩት ግን ከ3 ሺሕ የማይበልጡ ነበሩ ብለዋል።
በመሆኑም አደጋን ከመቀነስና የትራንስፖርት አገልግሎቱን የተሳለጠ ከማድረግ አንፃር ሌሎች ለአሰራር አስቸጋሪ የነበሩ ጉዳዮች በሙሉ በመመሪያ እንዲስተካከሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ በመተካት ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ሥራ በስፋት እየተሰራበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክ ለመቀየር የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱ ተገለጸ
በኢትዮጵያ ከ42 ሺሕ በላይ ምዝገባ ያጠናቀቁ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ ተብሏል
