የካቲት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ሰላማዊ ለማድረግ የተለያዩ የመፍትሄ ሀሳቦችን መመለከት ያስፈልጋል ሲሉ አሐዱ ያነጋገራቸው የዓለም አቀፍ ግኙነት ባለሙያዎች ገልጸዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት የቀድሞ ኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለአልጀዚራ በላኩት ፅሁፍ የኤርትራ መንግሥትን ወቅታዊ ሁኔታ በማንሳት፤ 'በቀጠናው አሉታዊ ተፅእኖ ለማምጣት የሚጥር መንግሥት' መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ይህንን የእርሳቸውን ንግግር ተከትሎም የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ለቀድሞ ፕሬዝዳንቱ ምላሽ የሚሆንና ሁለቱ ሀገራት ያሉበትን ሁኔታ የሚያሳይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ ሀገራት የተለያዩ የዜና አውታሮች በኩል ያልተረጋጡ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ሲሆን፤ "የኤርትራ ተቃወሚ ቡድን ብርጌድ ንሓመዶ በአዲስ አበባ ቢሮ ሊከፍት ነው" የሚል መረጃን ጨምሮ "ኤርትራ መንግሥት ከህወሓት አንዱ ቡድን ጋር ንግግር እያደረገ ነው" የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡
አሐዱም "ለመሆኑ እንዲህ ያሉ በሀገራት መካከል የሚስተዋሉ መወቃቀሶችና ውንጀላዎች ሁለቱ ሀገራት ከዛሬ ሰባት ዓመት ወደ ነበሩበት የመቃቃር ስሜት ይመለስ ይሆን?" ሲል የዓለም አቀፍ ግኙነት ባለሙያዎች ጠይቋል፡፡
አሐዱ ያነጋራቸው የቀድሞ ዲፕሎማት ዶክተር ተሾመ ሰብሮ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ የኤርትራ የጦር እንቅስቃሴ አካሄድ ተገቢ አለመሆኑን ያነሱ ሲሆን፤ "ይህንን የኢትዮጵያ መንግሥት በቸልታ ማለፍ የለበትም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በቀይ ባህር ዙሪያ እና በቀጠናው ያለው ውጥረትን በሚመለከት መንግሥት በጥንቃቄ መመልከት ያለበት መሆኑን ያነሱም ሲሆን፤ "ሁሉም ሃይሎች ንቁ መሆን አለባቸው" ብለዋል፡፡
ሌላኛው የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ባለሙያ እያሡ ሀይለ ሚካኤል በበኩላቸው፤ "እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች በሀገሪቱ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ናቸው" ብለዋል፡፡
በተለይም ከዚህ ቀደም የባድመ ግጭትን ተከትሎ ከዛም የአልጀርስ ስምምነት ላይ የነበረው ጉዳይ እና ወደ ሰላም የመጣው ሂደት የቅርብ ግዜ ትውስታ መሆኑን ያነሳሉ፡፡
አክለውም "በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጉዳዮችን ከጦርነት መለስ መፍታት ከተፈለገ ይፋዊ የሆነ ግጭት ውስጥ ባይሆኑም እንኳን፤ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ድርድር ማድረግ ይገባል" ብለዋል፡፡
"ሁለቱ ሀገራት በምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን ኢጋድ በኩልም ጉዳዮችን የሚመለከቱበት ሁኔታ መታየት አለበት" ያሉም ሲሆን፤ በቀጠናው ላይ ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ የድንበር ጉዳዮች መፈታት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የባድመን ጦርነት ተከትሎ ለ20 ዓመታት በከፍተኛ ውጥረት ላይ ቆይተው የነበረ ሲሆን፤ በ2010 ወደ ሰላም መምጣታቸውን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሰላም ኖቤል ሽልማት መሸለማቸው የሚታወስ ነው፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር የመፍትሄ ሀሳቦችን መመለከት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
