የካቲት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል በተለያዩ እርከን ላይ በሚገኙት ፍርድ ቤቶች የሚሰሩና እስከ ትናንት የካቲት 16 ቀን 2017 ድረስ በእስር ላይ የነበሩ ሁሉም ዳኞች ከእስር መለቀቃቸውን የክልሉ ዳኞች ማኅበር አስታውቋል።

ማኅበሩ ከአሁን በፊት በክልሉ ዳኞች ላይ የሚፈጸመው እስር እንዲቆም፣ የታሰሩት ዳኞች እንዲፈቱ እና የዳኞች ያለመከሰስ መብትም የሕግ ጥበቃ እንዲያገኝ ለአብክመ ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ ለክልሉ ምክር ቤት እና ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የታሰሩ ዳኞችን ዝርዝር የያዘ ደብዳቤ ማቅረብን በመግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮች ከተቋማዊ ለውጡ እና ከዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ጎን ለጎን ማኅበሩ ባቀረባቸው ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ገልጿል።

በዚህም መሠረት የዳኞችን ያለመከሰስ መብት የፍርድ ቤት ማጠናከሪያ አዋጅ ለክልሉ ምክር ቤት በማቅረብ፤ ባለፈው ሳምንት በምክር ቤቱ ጥበቃ እንዲያገኝ መደረጉን ማኅበሩ ለአሐዱ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በእስር ላይ የሚገኙ ዳኞችም እንዲፈቱ ሲደረግ በነበረው ጥረት መሠረት፤ ትናንትን ጨምሮ ባለፈው ሳምንት ሁሉም በእስር ላይ የነበሩ ዳኞች ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉን ገልጿል።

ማኅበሩ በዳኞች ላይ የሚፈጸመው እስር፣ እንግልት እና ወከባ የዳኝነት ነጻነትን በግልጽ የሚፃረር ከመሆኑም በላይ የሰብዓዊ መብቶች እንዳይከበሩ እና የሕግ የበላይነት እንዳይረጋገጥ የሚያደርግ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ተግባር መሆኑን በመግለጫው አመላክቷል።

ይህ አይነቱ ድርጊት እንዲቆም መስራት የሕግ ተርጓሚው ወይንም የፍርድ ቤቱ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፤ የሕግ አውጭው፣ የሕግ አስፈፃሚው እና የአጠቃላይ ማህበረሰቡም ድርሻ መሆኑንም አስታውቋል።

በመሆኑም የክልሉ ዳኞች ማኅበር ወደፊት በዳኞች ላይ የሚፈጸም እስር ጨርሶ እንዳይኖር፣ ለዳኞች የተሰጠው የመብት ከለላም በተገቢው መልኩ ሥራ ላይ እንዲውል ጠይቋል።

በክልሉ በተደረገ ጥናት መሰረት፤ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የትኛው ታጣቂ ሃይል እንደገደላቸው ሳይታወቅ ሦስት ዳኞች ስለመገደላቸው መረጋገጡን የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ብርሃኑ አሰፋ ከዚህ ቀደም ለአሐዱ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ