የካቲት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አገልግሎት ላይ የዋለው የወንጀል ጥቆማ መስጫ የሞባይል መተግበሪያ ችግሮችን እየቀረፈ ቢገኝም፤ በርካቶች እየተገለገሉበት አለመሆኑ ተነግሯል።

"የሞባይል መተግበሪያው ዜጎች በየትኛውም ቦታ ሲፈጸም የሚያዩትን ወንጀል በስልክ አማካኝነት በቀላሉ መጠቆም የሚያስችል ነው" ያሉት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ጄይላን አብዱ፤ መተግበሪያው በሥራ ላይ ከዋለ ወዲህ የወንጀል ድርጊቶችን መቆጣጠርና መቀነስ እንደተቻለ ለአሐዱ ተናግረዋል።

"ይሁን እንጂ የሞባይል መተግበሪያውን ጠቀሜታ ተረድተው እየተገለገሉበት የሚገኙ ዜጎች ጥቂት ናቸው" ብለዋል።

ይህም በግንዛቤ ማነስ ወይንም መተግበሪያው መኖሩን ባለማወቅ የተከሰተ ክፍተት መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ስለ ሞባይል መተግበሪያው ዜጎች የጠለቀ እውቀት እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በሥራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መተግበሪያ ዜጎች ሲፈፀም የሚያዩትን ወንጀል በፎቶ፣ በቪዲዮ፣ በድምፅ እና በሌሎች አማራጮች በማስቀረት ወደ ፖሊስ ጣቢያዎች መሄድ ሳይጠበቅባቸው በቀላሉ ጥቆማ ማቅረብ የሚያስችል ነው፡፡

በተጨማሪም መተግበሪያው ወንጀልን ከመጠቆም ባሻገር ወቅታዊ የትራፊክ እና ወንጀል ነክ መረጃዎችንም እንደሚቀርቡበት ተገልጿል።

የወንጀል ድርጊትን በስልክ አማካኝነት ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥቆማ ለመስጠት የሚያስችለው ይህ የሞባይል መተግበሪያ፤ የተጠቆመው የወንጀል ድርጊት የደረሰበትን የምርመራ ሂደት ለመከታተልም ዕድል ይሰጣል፡፡

በተጨማሪም ለዐይነ ስውራን እና መስማት ለተሳናቸው ምቹ አገልግሎት እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፤ ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ እንደሚሰጥም ተመላክቷል፡፡

ይህም መተግበሪያ የተለያዩ የቋንቋ አማራጮችን ማለትም፤ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ አፍ ሶማሊ እና እንግሊዝኛን በውስጡ ይዟል፡፡

ይህንንም መተግበሪያ ከአፕ ስቶር እና ከጎግል ፕሌይ ስቶር https://shorturl.at/ZAEhq በማውደር፤ መጠቀም እንደሚቻል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በአበረ ስሜነህ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ