የካቲት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኤስ.ኦ.ኤስ የሕጻናት መንደሮች ወጣቶች ማኅበር 100 ለሚጠጉ ወጣቶች በተለያዩ የሥራ መስኮች የሥራ እንዲያገኙ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፤ በዚህም በተቋሙ ውስጥ የሥራ ቅጥር ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ አጫጭር ኮርሶችን እንዲያገኙና የአነስተኛ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዱሆኑ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ይህንን የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለው የማኅበሩ አጋር ከሆነው፤ ከቀድሞው የኤስ.ኦ.ኤስ የሕጻናት መንደሮች ወጣቶች ማኅበር በአዲስ አበባ፤ "ሊቭ ኖ ዩዝ ቢሃይንድ ፕሮጀክት" ጋር በመተባበር መሆኑን የማኅበሩ ፕሬዝደንት አቶ እዮብ በቀለ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች በተለያዩ መንደሮች እንደማደጋቸው አኳያ፤ የቅርብ የሆነ ቤተሰብ ስለማይኖራቸው፤ በአንድም በሌላ መብታቸው ሊጋፉ የሚችሉ የትኛውንም የመንግሥት ፖሊሲዎችን ጨምሮ፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች ጾታዊ ትንኮሳ የሚደርስባቸው ከሆነ ማኅበሩ ከሚመለከታቸው የመንግሥትና የግል ተቋማት ጋራ በጋራ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

ከዚህም የሚዘል ከሆነ ጠበቃ እስከማቆም ድረስ በመሄድ መብታቸው ለማስከበር አቅዶ እየተቀሳቀሰ መሆኑን ያስረዱት የማህበሩ ፕሬዝዳንት፤ እንዲሁም በጤና እክል ሲገጥማቸውም በቂ የሕክምና ድጋፍ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ ከተመሰረተ 3 ዓመትን ያስጠረ ሲሆን፤ እስካሁን ድረስ በ11ዱም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች እየሰራ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ እስካሁን ድረስ ማኅበሩ ያልደረሰባቸው ቦታዎች ላይ አድማሱን በመስፋት የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የእውቀት ማስፋፋት እንዲሁም የተለያዩ የገንዘብ ድጋፎችን ለወጣቶች ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የማኅበሩ ግቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለአለፉት ሦስት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሲሰራ መቆየቱን ያስረዱት ፕሬዝዳንቱ፤ ነገር ግን በቀጣይ አድማሱን በማስፋት በመቀሌ፣ በሀረር እና በሃዋሳ ከተሞች ጨምሮ ማኅበሩን በማስፋፋት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቀጣይ ለመስራት ቢሮዎች እየተከፈቱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ነገር ግን ይህን የማህበሩን አቅም ለማሳደግ፤ሁሉም ዜጋ የሚችለውን ሁሉ በእውቀት፣ በጉልበት እንዲሁም በገንዘብ መልክ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አቶ እዮብ በቀለ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ