የካቲት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል ግቢ ውስጥ፤ ውሃ በአቆረ ጉድጓድ ውስጥ ዋና ለመዋኘት የገቡ ሦስት ታዳጊዎች ሕይወት ማለፉን የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ታዳጊዎቹ ትላንት እሁድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ኳስ ሲጫወቱ ቆይተው በዕጽዋት ማዕከሉ ጊቢ ውስጥ ባለው ውሃ በአቆረ ጉድጓድ ውስጥ ዋና ለመዋኘት ገብተው ሕይወታቸው ማለፉን፤ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል፡፡
የኮሚሽን መ/ቤቱ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችና ጠላቂ ዋናተኞች የታዳጊዎቹን አስከሬን አውጥተው ለፖሊስ ያስረከቡ ሲሆን፤ የታደጊዎቹ ዕድሜ ሁለቱ የ13 ዓመት እንዲሁም አንደኛው ደግሞ 16 ዓመቱ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ በአንዳንድ አካባቢዎች በተቆፍረው ውሃ ባቆሩ ጉድጓዶች ውስጥ ዋና ለመዋኘትና ለመታጠብ በሚል በተለይ ታዳጊዎችና ወጣቶች እየገቡ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ስለሆነም ጉድጓዱን የቆፈሩና በውሃ የሚጠቀሙ አካላት ተገቢውን አደጋን ቀድሞ የመከላከል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በአዲስ አበባ ውሃ በአቆረ ጉድጓድ ውስጥ ዋና ለመዋኘት የገቡ የሦስት ታዳጊዎች ሕይወት አለፈ
