የካቲት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) "የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን" በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የቆየው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ፤ በተለያዩ አህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።
ከነዚህም የአፍሪካ ሕብረት ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ የማካካሻ ፍትህ፣ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ለማግኘት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች፣ አህጉራዊ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የማካካሻ ፍትህ አጀንዳዎች ላይም ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ በተለይም ከቀኝ ግዛት እና የባርያ ንግድ ጋር ተያይዞ በተፈጸመው ታሪካዊ ኢ-ፍትሀዊነት እና በደል ካሳ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የማካካሻ ፍትሕ ግልጽ ያልሆነ እና ኢትዮጵያን የሚመጥን ስላለመሆኑ ተገልጿል።
ስለ ማካካሻ ፍትሁ ተግባራዊነት እና የኢትዮጵያን አካሄድ በተመለከተ አሐዱ ያነጋገራቸው የዲፕሎማሲ ምሁርና የቀድሞው ዲፕሎማት ዳያሞ ዳሌ፤ ከዚህ ቀደም በአህጉሪቱ በተለያዩ የአዉሮጳ ሀገራት የተደረጉ በደሎችን በተለይም የባርያ ንግድ በሕዝቦቻቸዉ ላይ ለተፈጸመባቸዉ እና ግፍ ለተካደባቸዉ ሀገራትን ኢላማ ያደረገው የማካካሻ ፍትሁ በመርህ ደረጃ መነሳቱ መልካም መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም "ኢትዮጵያ ለጥቁሮች የነጻነት ችቦን ያበራች ቀዳሚዋ ሀገር እንደመሆኗ በሕብረቱ የተነሳውን የካሳ ጥያቄ ማቀንቀኗ በጥሩ የሚታይ ነው" ያሉ ሲሆን፤ "ቢሆንም ኢትዮጵያ በቀኝ ያልተገዛች በመሆኑ በዚህ መንገድ የካሳ ጥያቄዎችን የምትጠይቅበት የሕግ አካሄድ የለም" ብለዋል፡፡
በጉዳዩ አስተያየታቸውን የሰጡት ሌላኛው የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ጥላሁን ሊበን በበኩላቸው የማካካሻ ጥያቄ በአፍሪካውያን ሲጠየቅ ይህ ለመጀመሪያ ግዜ ስላለመሆኑ ገልጸው፤ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ መሰል ጥያቄዎች እና ንግግሮች ተደርገው ተግባራዊ ሳይደረጉ መቅረታቸውን እና አሜሪካ፣ ብሪቴን እና ሌሎችም ሀገራት 'የዕንቢታ መልስ' መመለሳቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ታዲያ "የማካካሻ ፍትሁ ተፈጻሚ የሚሆንበት አካሄድ በራሱ አጠያያቂ ነው" ያሉ ሲሆን፤ "የማካካሻ ፍትህ የሚያስፈልጋቸዉ የአፍሪካ ሀገራት የትኞቹ ናቸዉ? የሚጠየቁትስ የትኞቹ ናቸው? የሚለው እንዲሁም ሕብረቱ ተከታትሎ ያስፈጽማል ወይ? የሚለውንም ጥያቄ የሚያስነሳ ነው" ብለዋል፡፡
አክለውም "በግልጽ ካሳ የሚጠየቀውስ ማነው? የሚለው በራሱ የተለየ ሆኖ አለመቅረቡ በተግባራዊነት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ክፈተት ነው" ያሉ ሲሆን፤ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት እና የካሳ ጥያቄ አካሄድ በራሱ በቀኝ ላልተገዛች ሀገር ግርታን የሚፈጥር እና ኢትዮጵያን የማይመጥን መሆኑን አንስተዋል።
የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ባለሙያዎቹ አክለውም፤ "ሕብረቱ በዘንድሮው ጉባኤ መሰረታዊ በሆኑ አፍሪካዊ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያዎች ቢያደርግም ተግባራዊነቱ እና አካሄዱ ላይ በጥንቃቄ ሊጤን ይገባል" ያሉ ሲሆን፤ እንደ ሕብረት የጸደቁትን ጉዳዮች ተከታትሎ የሚያስፈጽም ሊሆን ይገባል ብለዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በአፍሪካ ይተገበራል የተባለው የማካካሻ ፍትሕ ግልጽ ያልሆነ ውሳኔ ነው ሲሉ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ገለጹ
