የካቲት 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የማኅበራዊ ፍትሕ ቀን "ፍትሐዊ ሽግግርን ማጠናከር ለተረጋጋ ቀጣይነት" በሚል ጭብጥ ትናንት የካቲት 13 ቀን 2017 በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሮ ውሏል።
ዓለም ከከርሰ ምድር የነዳጅ ኃይል ተጠቃሚነት ወደ አረንጓዴ ኃይል ተጠቃሚነት እያደረገች ያለው ሽግግር፣ በአንጻሩ ዓለም የገጠማት ያልተረጋጋ የምጣኔ ሀብት ሁኔታን እና ይህንን ተከትሎ ከተፈጠረው የምጣኔ ሀብት ኢ-ፍትሐዊነት ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ችግሮች ቀንኑ አስመልክቶ ከተነሱ ሀሳቦች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

አሐዱም ይህን አስመልክቶ "በኢትዮጵያ የማህበራዊ ፍትህ ተደራሽነት እና ተፈፃሚነት ምን ያህል ነው?" ሲል የሕግ ባለሙያዎችን ጠይቋል።
የሕግ ባለሙያው ካሳሁን ሙላቱ፤ "የማህበራዊ ፍትህ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በሀገሪቷ የሚፈጠር ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ አገልግሎት ማለትም ትምህርት፣ ጤና እና መሰረተ ልማት በጋራና በእኩልነት ተጠቃሚ መሆን ማለት ነው" ብለዋል።
ይህም በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ብሎም ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ መቀመጡን ያነሱት የሕግ ባለሙያው፤ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ሌሎች ችግሮች ማህበራዊ ፍትህ እንዳይሰፍን ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።
"በሕብረተሰቡ ዘንድ መብትን አውቆ መጠየቅና ግዴታን መፈጸም ወደኃላ የቀረንበት ነው" ሲሉም አክለዋል።
የቀደመውን የሕግ ባለሙያ ሃሳብ የሚጋሩት ሌላው የሕግ ባለሙያ ባንተወሰን ግርማ በበኩላቸው፤ "ማህበራዊ ፍትሕ በኢትዮጵያ ለሁሉም ተደራሽ ሆኗል ማለት አያስችልም" ሲሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን ማህበራዊ ፍትህን ተደራሽ ለማድረግ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አንስተዋል።
በማህበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤን ለመፍጠር ከታች ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ መንግሥት ተቋማት መሰራት እና በተቻለ መጠን ማህበራዊ ፍትህን ለማስፈን ጥረት መደረግ እንዳለበትም ገልጸዋል።
የዓለም የማኅበራዊ ፍትሕ ቀን በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እ.ኤ.አ በ2007 የተቋቋመ ሲሆን፤ ከ2009 ጀምሮ ቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የካቲት 13 ተከብሮ ይውላል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በማህበራዊ ፍትህ ዙሪያ በተለያዩ ሀገራት በዜጎች ላይ በግልም ሆነ በተናጠል የሚፈጸሙ ኢ-ፍትሀዊ ድርጊቶች እየጨመሩ መምጣቸውን በመጠቆም፤ ለዓለም ሰላም ማሕበራዊ የዜጎች ፍትሕ ማስፈን አስፈላጊ መሆኑን አሳስቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ