የካቲት 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረደ 9 ልዩ ቦታው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አካባቢ፤ የሜትር ታክሲ አገልግሎት ፈላጊ በመምሰል አሽከርካሪዎችን በመደብደብ 2 ተሽከርካሪዎችን ይዘው የተሰወሩ ሁለት ተከሳሾች በሁለት መዝገብ እያንዳንዳቸው በ22 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

ሀዱሽ አባዲ እና ብርሀኑ ኃይሌ የተባሉ ተከሳሾች የሜትር ታክሲ አገልግሎት ፈላጊ በመምሰል የተሽከርካሪ ስርቆት ወንጀል የፈፀሙት ሐምሌ 21 ቀን 2015 ዓ/ም ከሌሊቱ 8፡00 ሠዓት ገደማ መሆኑ ተገልጿል።
ተከሳሾቹ የግል ተበዳይ ወጣት መልሳቸው ሀበሻ አሻግሬ የተባለን በወቅቱ ሲያሽከረክር የነበረውን ኮድ 3A 75963 አ/አበባ የሆነ ቪትስ ተሽከርካሪ የዋጋ ግምቱ 1ሚሊዮን 4 መቶ ሺ የሚያወጣ መንገድ ላይ ካስቆሙት በኋላ ወደ ገርጂ ሮባ ዳቦ እንዲወስዳቸው መነጋገራቸው ተገልጿል።
በኋላም መኪናው ውስጥ ከገቡ በኋላ የግል ተበዳይን ከኋላ አንቀው በመያዝና 'ከተናገርክ እንገልሀለን' በማለት እጅና እግሩን አስረው 2 የሞባይል ስልኮች የዋጋ ግምታቸው 35 ሺሕ ብር የሆነ ከወሰዱበት በኋላ ጨለማ ቦታ ላይ በመገፍተር ተሽከርካሪውን ይዘው ተሰውረዋል።
በመቀጠልም ተሽከርካሪውን ለሌላ ግለሰብ አሳልፈው በመሸጥ ላይ እያሉ ፖሊስ ባደረገው ክትትል ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ንብረቱን ለባለቤቱ ማስመለሱን ገልጿል።
በሌላ በኩል ከላይ የተጠቀሱት ተከሳሾች ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ/ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረደ 4 ልዩ ቦታው ለም ሆቴል ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከሌሊቱ 5:00 ሠዓት ገደማ ተመሳሳይ የውንብድና ወንጀል መፈጸማቸው ተገልጿል።
ይኸውም በረከት ሙሉጌታ የተባለን የግል ተበዳይ በወቅቱ ኮድ 3B 51731 አ/አ የሆነ ቪትስ ተሽከርካሪ የዋጋ ግምቱ 1 ሚሊዮን 200 ሺሕ ብር የሚያወጣ እያሽከረከረ እያለ ተከሳሾቹ የራይድ አገልግሎት ፈላጊ በመምሰል ግለሰቡን አስቁመው ከ 22 ወደ ለም ሆቴል አድርሰን በማለት መሳፈራቸው ተመላክቷል፡፡
በኋላ ሐዱሽ አባዲ የተባለው ገቢና በመቀመጥ ሌላኛው ብርሀኑ ኃይሌ የተባለው 2ኛ ተከሳሽ ከኋላ ወንበር ላይ በመቀመጥ ለም ሆቴል አካባቢ ሲደርሱ አሽከርካሪውን ወደ መንደር ውስጥ እንዲያስገባቸው ይነግሩታል።
የግል ተበዳይም ወደ ተባለው ቅያስ መንገድ እየገባ ሳለ ከኋላ ወንበር ላይ የተቀመጠው ተከሳሽ የግል ተበዳይን አንቆ በመያዝ፣ ቢላ በማውጣትና 'ከተናገርክ አርድሀለሁ' ብሎ በማስፈራራትና በመደብደብ በወቅቱ ይዞት የነበረውን ከ4 ሺሕ ብር በላይ እና ሳምሰንግ ሞባይል የዋጋ ግምት 10 ሺሕ የሚያወጣ፤ እንዲሁም የዋጋ ግምቱ 18 ሺሕ ብር የሆነ ላፕቶፕ ከወሰዱበት በኋላ ከመኪናው ላይ ገፍትረው በመጣል ተሽከርካሪውን ይዘው ተሰውረዋል።
ይህንንም ተከትሎ ጥቆማው የደረሰው የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስም ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋልና ንብረቱን ለባለቤቱ ለማስመለስ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል።
ሁለቱም ተከሳሾች የሰረቁትን ተሽከርካሪ ይዘው ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ወደ ትግራይ ክልል በመውሰድ የተሽከርካሪውን ሻንሲ እና የሞተር ቁጥርን በመቀየር እንዲሁም፤ ትክክለኛውን የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3B51731 አ/አ የሚለውን ወደ ኮድ 203493 ትግ በመቀየር ፊሊሞን ኃይሌ ለተባለ ግለሰብ በ1 ሚሊዮን ብር መሸጣቸው ተመላክቷል፡፡
በዚህም መሰረት የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ከትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ተሽከርካሪውን በማስመለስ በዐቃቤ ሕግ በኩል በተከሳሾች ላይ ክስ እንዲመሠረትባቸው ተደርጓል።
የተከሳሾቹን የወንጀል መዝገብ ሲከታተል የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ጥር 9 ቀን 2017 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተከሳሾች ሐዱሽ አባዲ እና ብርሀኑ ኃይሌ ግለሰቡ ላይ ባደረሱበት አካላዊ ጉዳትና በወሰዱት ንብረት በከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ እያንዳንዳቸው በ11 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
በተጨማሪም በ2ኛ መዝገብ ጥር 13 ቀን 2017 ዓ/ም በተመሳሳይ እያንዳንዳቸውን በ11 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል።
ተከሳሾቹ በሁለቱም የክስ መዝገብ በድምሩ 22 ዓመት ጽኑ እስራት እንደተወሰነባቸውም የክስ መዝገቡ አስረድቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ