የካቲት 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በመስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን የባሮ ወንዝ ጂካዎ ጊዜያዊ ድልድይን ጥሶ የገባው አምቡላንስ ተሽከርካሪ፤ ከወራት ፍለጋ በኋላ በውስጥ ያሉ 5 አስከሬኖችን እንደያዘ መገኘቱን የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኮንግ ፔል ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ አንቡላንሱ አሽከርካሪውን ጨምሮ ሰባት ሰዎችን በመያዝ ከጋምቤላ ከተማ ተነስቶ ወደ ኑዌር ዞን ሲጓዝ ጅካዎ ድልድይ ጥሶ ወንዝ ውስጥ መግባቱን ይታወሳል።
በዚህም የ7 ሰዎች ሕይወት አልፎ የነበረ መሆኑን ለአሐዱ የተናገሩት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አምስት ወራት ገደማ ከተቆጠሩ በኋላ አንቡላንሱ በውስጡ አምስት አስከሬኖችን እንደያዘ መገኘቱን ተናግረዋል።

በወቅቱ በደረሰው የመኪና አደጋ የሟቾችን አስከሬን ከወንዝ ውስጥ ለማውጣት ጥረት ሲደረግ ቢቆይም፤ የባሮ ወንዝ ከመጠን በላይ በመሙላቱ ምክንያት በተለያየ ጊዜ የሁለት ሰዎች አስክሬን ብቻ መገኘቱን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ የባሮ ወንዝ የውሀ መጠን መጉደሉን /መቀነሱን/ ተከትሎ፤ አምስት ወራት ገደማ ከተቆጠሩ በኋላ ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም አምቡላንሱ በውስጡ አምስት አስክሬኖችን እንደያዘ መገኘቱን ኃላፊው ለአሐዱ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ