የካቲት 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ቀሺ ገጠር ቀበሌ ልዩ ስፍራው የምታ ተብሎ በሚጠራበት መንደር 'በፖሊስ አሳስረህኛል' በሚል ቂም በመነሳት ግለሰብ ላይ የግድያ ወንጀል የፈፅሙ እና አስክሬን የደበቁ ስድስት የአንድ ቤተሰብ አባላት በእስራት መቀጣታቸውን የዞኑ ፍትሕ መምሪያ አስታውቋል፡፡
ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ላይ ስድስት የአንድ ቤተሰብ አባላት የግል ተበዳይን መንገድ በመጠበቅ ድምፅ በሌለው ጦርና ገጀራ የግድያ ወንጀል መፈማቸውን በመምሪያው የልዩ ልዩ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ወ/ሪት ምኞት አበበ ተናግረዋል፡፡
የወንጀል ደርጊቱን የፈፀሙት በቁጥር ስድስት ሲሆኑ፤ አንደኛ ተከሳሽ ወሰኔ ቡሾ ሁለተኛ ተከሳሽ ቡሾ ኃይሌ ሦስተኛ ተከሳሽ ታመኔ ቡሾ አራተኛ ተከሳሽ ወዳጆ ቡሾ አምስተኛ ተከሳሽ ቡዛየሁ ቡሾ እና ስድስተኛ ተከሳሳሽ ማሙሽ ቡሾ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የዴቻ ወረዳ ፖሊስ ስድስቱን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር አድርጎ ያጣራውን የምርመራ መዝገብ መነሻ በማድረግ የዞኑ ዐቃቤ ሕግ በክስ አንድ ላይ እንዳመላከተው፤ አንደኛ ተከሳሽ ወሰኔ ቡሾ የግል ተበዳይን መንገድ በመጠበቅ " 'ስልኬን እና ገጀራ ሰርቀሀል' ብለህ በፖሊስ አሳስረህኛል" በሚል ቂም በያዘው ጦር የግራ እጁ ላይ እና በቀኝ በኩል ጎኑ ላይ አንድ ጊዜ ሲወጋው በወደቀበት በገጀራ የግራ አይኑ ቅንድብ ላይ እና መንጋጋዉ ላይ በመቁረጥ ሕይወቱ እንዲያልፍ ማድረጉ በክሱ ተጠቅሷ።
እንዲሁም ሁለተኛ ተከሳሽ ቡሾ ኃይሌ በበኩሉ ይዞት በነበረው ገመድ የሟቹን አንገቱን እና መንጋጋዉን በማሰር አስክሬኑን 400 ሜትር መሬት ለመሬት በመጎተት ጫካ ውስጥ መደበቁንና ዐቃቤ ሕግ አንደኛ እና ሁለተኛ ተከሳሾችን ሰው በመግደል ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
ዐቃቤ ሕግ በ3ኛ እስከ 6ኛ ባሉ ተከሳሾችን የግል ተበዳይ ላይ ሁለቱ ግለሰቦች የግድያ ወንጀል ሲፈፅሙ እና በአስክሬኑን አንገት ገመድ አድርገው አስክሬኑን ለመሰወር ተባብረዋል እንዲሁም፤ ጎትተው ወስዶ ጫካ ውስጥ ጥለዋል በሚል አራቱን ግለሰቦች በፈፀሙት መሸሸግና አለመርዳት ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
የካፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዞኑ ዓቃቤ ሕግ በሁለት ክሶች ክስ መስርቶ ያቀረበውን መዝገብ አስቀርቦ ግራ ቀኙን አስቀርቦ በማከራከር 6ቱንም ተከሳሾች በፈፀሙት የግድያ ወንጀል ክስ በማስረጃ በማረጋገጡ በሁሉም ላይ የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል።
በዚሁ መሰረት የካፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባስቻለዉ የወንጀል ችሎት፤ አንደኛ ተከሳሽ ወሰኔ ቡሾ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት ሁለተኛ ተከሳሽ ቡሾ ኃይሌ በ7 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኗል።
ከሦስተኛ እስከ ስድስተኛ ያሉ ተከሳሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው በ6 ወር ቀላል እስራት እዲቀጡ ዉሳኔ እንደተላለፈባቸው ዐቃቤ ህግ ምኞት አበበ ተናግረዋል ሲል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዘግቧል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
'በፖሊስ አሳስረህኛል' በሚል ቂም በመነሳት የግድያ ወንጀል የፈፅሙ እና አስክሬን የደበቁ ስድስት የአንድ ቤተሰብ አባላት በእስራት መቀጣታቸውን ተገለጸ
