መጋቢት 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በብልሽት ምክንያት ለታካሚዎች አገልግሎት መስጠት አቁሞ የነበረው የካንሰር የጨረር ሕክምና መስጫ መሳሪያ ተጠግኖ ዳግም ወደ ሥራ መመለሱን ጥቁር አንበሳ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታውቋል።

የጨረር ሕክምና መስጫ መሳሪያው ከአንድ ዓመት ከ6 ወር በላይ ተበላሽቶ በመቆየቱ፤ ታካሚዎች የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ አሐዱ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል፡፡

"ታዲያ በአሁኑ ወቅት በርካታ ተገልጋዮች የጨረር ሕክምና የሚፈልጉ በመሆኑ የጥገና ሥራው ከምን ደረሰ? ወደ አገልግሎትስ ተገብቷል ወይ?" ሲል አሐዱ የሆስፒታሉን የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሰለሞን ጠይቋል።

ኃላፊው በሰጡት ምላሽም በሆስፒታሉ ለታካሚዎች አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ሁለት የካንሰር ጨረር ሕክምና መስጫ መሳሪያዎች በብልሽት ምክንያት መሥራት አቁመው እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት አንደኛው አስፈላጊው ጥገና ተደርጎለት ወደ ሥራ መመለሱን ተናግረዋል።

አክለውም ሆስፒታሉ የመጨረሻ ሪፈራል ሆስፒታል እንደመሆኑ ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ታካሚዎች ስለሚጠቀሙበት በአገልግሎት አሰጣጥ ጫና ተበላሽቶ መቆየቱን የገለጹም ሲሆን፤ "አሁን አንዱ ተጠግኖ ዳግም አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል" ሲሉ ተናግረዋል።

ይህም ታካሚዎች 'የጨረር ሕክምና እያገኝን አይደለም' በሚል ለሚያነሱት ቅሬታ ምላሽ እንደሚሆንና፤ አሁን የጨረር ሕክምናውን እያገኙ መሆኑን ነግረዉናል፡፡

አሁን አገልግሎት መስጠት የጀመረው አንዱ የካንሰር ጨረር ሕክምና መስጫ መሳሪያም፤ በቀን ከ60 እስከ 70 ለሚሆኑ ታካሚዎችን አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ የሆስፒታሉ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል።

በዘላቂነት የሚስተዋለውን እጥረት ለመፍታትም ለጤና ሚኒስቴር የሕክምና መስጫ መሳሪያው እንዲገባ በተጠየቀው መሠረት እስገባ እየተጠበቀ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

አዲስ የሚገባው መሳሪያ የሚፈጠረውን ችግር ይፈታል ተብሎ እንደሚታሰብ አንስተው፤ የሆስፒታሉ ማኔጀመንት ከጤና ሚኒስቴር ጋር ተነጋግሮ መሳሪያዎች እንዲገባ ሂደት መጨረሱንም አስረድተዋል።

"ታካሚዎች እንዲህ አይነት ችግር ሲገጥም ተመሳሳይ የሕክምና ወደሚሰጡ ሆስፒታሎች በመሄድ ሕክምናውን ማግኘት አለባቸው" ብለዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ