የካቲት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የዝሆን ጥርስንና መሰል የዱር እንስሳት ውጤቶችን በሕገ-ወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ ግለሰቦች ለሕግ እየቀረቡ እንደሚገኝ፤ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በዚህም በሕገ-ወጥ መንገድ ዝሆኖች እንዳይገደሉና የዱር እንስሳት ውጤቶች ዝውውር እንዳይስፋፋ ሕግን የማስከበር ሥራ እየተሰራ መሆኑን፤ የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
በብሄራዊ ፓርክ ውስጥ የሚገኝ እና የመመናመን አደጋ የተጋረጠበትን የዝሆን ዝርያን ለማስቀጠልም ዝሆኖች ለሕገ-ወጥ አደን ተጋላጭ እንዳይሆኑ እና ጥርሳቸውም እናዳይዘዋወር የመከላከል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዚህም አሐዱ "በኬላዎች እና በአየር መንገድ በኩል ሕገ-ወጥ የዝሆን ጥርስ ዝውውር እንዳይካሄድ ያለው የቁጥጥር ሂደት ምን ይመስላል?" ሲል የጉምሩክ ኮሚሽንን ጠይቋል።
የኮሚሽኑ ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን አሰፋ በሰጡት ምላሽ በ15 ኬላዎች ላይ የቁጥጥር የሥራ ሂደት እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፤ በክትትል ወቅት የዝሆን ጥርስን በተለያዩ ሕገ-ወጥ መንገዶች ሲዘዋወርና ከሀገር ወደ ሀገር ለማሳለፍ ጥረት ሲደረግ በስፋት እንደሚስተዋል ተናግረዋል።
ሕገ-ወጥ የዝሆን ጥርስ ዝውውርን ለመቆጣጠር ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣንና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ከሕገ-ወጥ የዝሆን ጥርስ ዝውውር ጋር ተያይዞ በሚፈጸም ሕገ-ወጥ አደን ምክንያት፤ የዝሆኖች ቁጥር ከዕለት ወደ እለት እየተመናመነ እንደሚገኝና ህልውናቸውንም ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ እየወደቀ መሆኑ በተደጋጋሚ ይገለጻል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ባለስልጣኑ የዱር እንስሳት ውጤቶች በሕገ-ወጥ መንገድ የሚያዘዋዉሩ ግለሰቦችን ለሕግ እያቀረበ እንደሚገኝ አስታወቀ
