የካቲት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ለሱዳን ሕዝብ ሰላምና መረጋጋት በሁሉም መስክ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን የተናገሩት በሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ላይ የሚመክርና በኢትዮጵያ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በአፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ነው፡፡

በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ኢትዮጵያና ሱዳን ጎረቤት ሀገራት ብቻ ሳይሆኑ ጠንካራ ቁርኝት ያላቸው ሀገራት ናቸው" ብለዋል።

"ኢትዮጵያ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሱዳን ሕዝብ ጎን ትቆማለች፤ ባላት አቅምም የምታደረገውን የሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላልች" ሲሉም ድጋፋቸውን አረጋግጠዋል።

Post image

በዚህም ኢትዮጵያ ለሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ 15 ሚሊየን ዶላር ወይም 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መለገሷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

አክለውም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለሱዳን ዘላቂ ሰላም መስፈን እንዲሁም የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች ለሰላማዊ መፍትሄ እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በበኩሏ 200 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ሰጥታለች።

Post image

የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ለሱዳን አንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግም በመድረኩ ላይ አስታውቀዋል።

እንዲሁም ጅቡቲ፣ ሞሮኮ እና ሌሎችም ሀገራት በድምሩ 217 ሚሊዮን ዶላር ለሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ እያደረጉ ላሉት ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

Post image

በአሁኑ ወቅት ከሱዳን አጠቃላይ ሕዝብ 64 በመቶ የሚሆነው ድጋፍ እንደሚፈልጉ የተገለጸ ሲሆን፤ በሃገሪቱ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት 30 ሚሊዮን ሱዳናዊያን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚስፈልጋቸው ተመድ አስታውቋል።

Post image

በዚህ ጉባኤ ላይም የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼህ ሻክቡት ቢን ናህያን አልናህያን፣ የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ