የካቲት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ባለፈው የታሕሳስ ወር በተደረሰው ስምምነት መሰረት፤ የመጀመሪያውን ዙር የቴክኒክ ድርድርን ትናንት የካቲት 11 ቀን 2017 በቱርክ አንካራ አካሂደዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ዙሪያ በቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን አሸማጋይነት በተፈራረሙት የአንካራው ሥምምነት መሰረት ነው፤ የመጀመሪያውን ዙር የቴክኒካል ውይይት ያደረጉት።

ሀገራቱ ሀገራት ወደ ስምምነት ለማምጣት ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኘው ቱርክ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ፤ የቴክኒክ ድርድሩ የአንካራውን ስምምነት የተከተለ መሆኑን ገልጻለች።

Post image

በመጀመሪያው ዙር የቴክኒክ ድርድር ሁለቱም ልዑካን የአንካራው ስምምነት መፈጸም ላይ ያላቸን ቁርጠኝነት ያሳዩበት መሆኑም ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውይይቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ ልዑካኑ የአገራቱ መሪዎች በአንካራ ስምምነት ላይ ያስቀመጡትን ራዕይ ወደ ተግባር ለመቀየር እንዲሁም ለጋራ የዘላቂ ልማት ተጠቃሚነት መሠረት ለመጣል ተጨባጭ ሥራ መጀመራቸውን አስታውቋል።

ይህን የቴክኒክ ድርድር የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን በመሩት ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ወክለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቴዎስ እንዲሁም ከሶማሊያ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አሊ መሐመድ ኦማር ተገኝተዋል።

Post image

ሁለቱ ሀገራት መሪዎች በታሕሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ ባካሄዱት ድርድር፤ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ በኩል ዘላቂ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የወደብ አማራጭ በምታገኝበት አማራጭ ላይ የቴክኒክ ውይይቶችን ለመጀመር መስማማታቸውን ይታወሳል።

ስምምነቱን ለማስፈጸምም ከመጋቢት ወር 2017 በፊት የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የማመቻቸት ሥራ ይሰራል ተብሎ የነበረ ሲሆን፤ በ4 ወራት ውስጥ ደግሞ ሂደቱ ተጠናቆ ስምምነት እንደሚፈረም ተመላክቷል።

ይህንንም ተከትሎ የመጀመሪያው ዙር ቴክኒካል ውይይት በትናንትናው ዕለት ተካሂዷል፡፡ በሁለቱ ሀገራ መካከል የሚካሄደው ቀጣዩ የቴክኒክ ድርድርም ለመጋቢት 2017 ዓ.ም. እንዲካሄድ ቀጠሮ መያዙ ተገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ