የካቲት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ልዩ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ነገ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡
ለጨረታ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሪ መጠን 60 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን፤ ጨረታው ለሁሉም ባንኮች ክፍት እንደሚሆን ተነግሯል፡፡
ባንኩ ሐምሌ 2016 የተጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራምን ተከትሎ፤ የኢትዮጵያ የውጭ ክፍያ ሚዛን በተለይም የወጪ ንግድ፣ ሐዋላና የካፒታል ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል ማሳየቱን ገልጿል፡፡
በተለይም ከቅርብ ወራት ወዲህ ወርቅን ወደ ውጭ የመላክ ብቸኛ ሥልጣን ላለው ብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መጠን በመጨመሩ ምክንያት የባንኩ ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት እጅግ አበታች መሆኑን አመላክቷል፡፡
የብሔራዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ፍሰት መጨመር የሪፎርሙ ጥሩና አዎንታዊ ውጤት ቢሆንም፤ የማዕከላዊ ባንኩን ጥብቅ የገንዘብ ዕድገት ፖሊሲና የዋጋ ንረት ግብ ስኬት በማያደናቅፍ መልኩ ሊተገበር እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡

በመሆኑም ከባንኩ የወርቅ ግዥ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የገንዘብ አቅርቦት ዕድገት ለማገናዘብና በማዕከላዊ ባንኩ እጅ ካለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከፊሉን ለግሉ ዘርፍ በመስጠት በገበያው ላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሻሻል ባንኩ የተወሰነ የውጭ ምንዛሪ ለባንኮች በጨረታ ለመሸጥ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቀጣይ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ሁኔታን በቅርበት በመከታተል እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ሽያጮችን እንደሚያካሂድ በዛሬው ዕለት ባመጣው መግለጫ አመላክቷል፡፡
ይህም የባንኩን የዋጋና የውጭ ኢኮኖሚ መረጋጋት ለማስፈን ያስቀመጠው ስትራቴጂያዊ ግብ አካል መሆኑን አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ባንኮች በተቀመጠው መስፈርት እና የጊዜ ማዕቀፍ መሰረት በጨረታው እንዲሳተፉ ብሔራዊ ባንክ ጥሪ አቅርቧል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ