የካቲት 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እና በ46ኛው የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ፤ ኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄዋን እና አቋሟን ግልጽ ማድረግ አለባት ሲሉ አሐዱ ያነጋገራቸው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያዎች ገልጸዋል።
በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ ወደብ አማራጭ ውስጥ የማይገባና መሰረታዊ መሆኑን ማንጸባረቅ እንዳለባትም ባለሙያዎቹ አሳስበዋል።
"ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደብ አስፈላጊ ነው" ያሉት የቀድሞው ዲፕሎማት ደያሞ ዳሌ፤ "አስተማማኝ የሆነ ወደብ ማግኘቷ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማሳመን መቻል አለባት" ብለዋል።
እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጋር በተለያየ ምክንያት ቅሬታ ውስጥ የገቡ ሀገራት በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ወታደሮቻቸውን ማስፈር እንደሌለባቸው ኢትዮጵያ አቋማን ማንጸባረቅ እንዳለባት ገልጸዋል።
ሌላው አሐዱ ያነጋገራቸው የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ባለሙያው ጥላሁን ሊበን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት ለማድረግ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከርና በሰላማዊ መንገድ ወደብ ማግኘት እንደምትፈልግ አቁሟን ይፋ ማድረግ እንዳለባት አንስተዋል።
በተመሳሳይም "መንግሥት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የሚጠበቅበት ኅላፊነት ሊወጣ ይገባል" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ይበልጥ ለማጠናከርና ወደብ የምታገኝበት መንገድ ለማግኘት የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አክለውም "ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲዉ ጠንካራ እና ተሰሚነት ያላት ሀገር ለመሆን፤ በመጀመሪያ የውስጥ ሰላሟን ማረጋገጥ አለባት" ሲሉ አሳስበዋል።
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በመጪው የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም ፣ 46ኛው የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ደግሞ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ይታወቃል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የወደብ ጥያቄዋን እና አቋሟን ግልጽ ማድረግ አለባት ሲሉ ባለሙያዎች ገለጹ
