ጥር 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ለአሜሪካ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በተከላካይ መስመር የምትጫወተው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናኦሚ ግርማ፤ የዓለምን የሴት እግር ኳስ ተጫዋቾችን የዝውውር ዋጋ ክብረ ወሰን በመስበር ወደ ቸልሲ መዘዋወሯ ተሰምቷል፡፡
ከአባቷ ግርማ አወቀ እና ከእናቷ ሰብለ ደምሴ በአሜሪካ በሳንሆዜ ካሊፎርንያ ተወልዳ ያደገችው የ24 ዓመቷ ናኦሚ ግርማ፤ በአሜሪካ ከሚገኘው ከሳንዲዬጎ ዌቭ ክለብ ወደ ቼልሲ ለማዘዋወር 900 ሺሕ ፓውንድ ወይንም 1 ነጥብ 12 ሚልየን ዶላር እንደከፈለባት ታውቋል።
በዚህም መሰረት ናኦሚ በአውሮፓውያኑ እስከ 2029 ድረስ የሴቶች ሱፐር ሊግ መሪው ከሆነው ከሰሜን ለንደኑ ክለብ ጋር ቆይታ እንደሚኖራ ተነግሯል፡፡
ናኦሚ ግርማ የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ አገሯ ከብራዚል ጋር ለፍፃሜ ደርሳ ብራዚልን 1 ለ ባዶ በማሸነፍ ወርቅ ያስገኘች ሲሆን፤ በተጨማሪም ኮንካካፍ ጎልድ ዋንጫ እና ሺ ቢሊቭስ የተባለው ዋንጫ ባለቤት መሆን ችላለች።
እንዲሁም የዓለማችን ምርጥ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ተብላም የተመረጠች ሲሆን፤ በአሜሪካ ብሄራዊ ሴቶች እግር ኳስ ሊግ በ2020 የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋች በመባል እንዲሁም በ2023 የዓመቱ ምርጥ ሴት ተጫዋች በመባል ተሸልማለች።
በተጨማሪም በ2022 በአሜሪካ በምትጫወትበት የሴቶች ሊግ ምርጡ ተጫዋች ሆና የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝታለች።
በዚህም መሰረት ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ተከላካይ ናኦሚ ግርማ በከፍተኛ ዋጋ የተዘዋወረች የዓለማችን ውድ ሴት እግር ኳስ ተጨዋች በመሆን አዲስ ሪከርድ ማስመዝገብ ችላለች።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ