ጥር 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ በዛሬው ዕለት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በዚህም ልዩ ስብሰባው ላይ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ጋር ያደረጋቸውን ሁለት የብድር ስምምነቶችን አጽድቋል።

የብድር ስምምነቶቹ የፋይናንስ ዘርፉን ለማጠናከርና የመንግሥት አገልግሎትን ለማሻሻል የሚውሉ መሆኑ ተነግሯል።

የብድር ስምምነቶቹን አስመልክቶ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ጋር ያደረገችው የ700 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነትና ተወዳዳሪነት የበለጠ ለማሻሻል ያስችላል ብለዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፒታል አቅምን እንደሚያሳድግ ገልፀው፤ ብድሩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን አሰራር ለማዘመን እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት የዕዳ ጫናዋ እየቀነሰ መምጣቱንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያና ዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ለዘመናዊ የመንግሥት አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ70 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነትም ለምክር ቤቱ ቀርቧል።

ምክር ቤቱ በብድር ስምምነቶቹ ላይ ከተወያየ በኃላ ስምምነቶቹን በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።


#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ