ጥር 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ያለው መንገድ በተደጋጋሚ በትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ቅሬታ ሲያነሱበት የሚስተዋል ነው።

በተለይም አሸከርካሪዎች የመንገዱ መበላሸት ለጤና ጉዳት ብሎም የንብረት ጉዳት በሰፊው እንደሚያጋጥማቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።

በዚህም አሐዱ "የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍን ለማሳደግ ሲሰራ የመንገዱ ችግር እንቅፋት አይሆንም ወይ? ምን ለማድረግ ታስቧል?" ሲል የኢትዮ ሎጂስቲክስ ዘርፍ ማህበራትን ጠይቋል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ኤልሳቤት ጌታሁን "የጅቡቲ መስመር ሊፈታ ያልቻለ ችግር ሆኖብን ቀጥሏል" ሲሉ ገልጸዋል።

በቅርቡ ግን መፍትሔ ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት ፕሬዝዳንቷ፤ "አሁንም ግን በጋላፊ በኩል ያለው መንገድ ችግር ያለበት በመሆኑ አማራጭ መንገዶችን መጠቀም ያስፈልጋል" ብለዋል።

አክለውም ለጅቡቲ መንግሥት በመንገዱ ላይ ያለውን ችግር አቅርበናል ያሉ ሲሆን፤ ጉዳዩን እየተመለከተው ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በሚፈለገው ፍጥነት ግን እየሄደ አለመሆኑን አንስተዋል።

ይህንኑ ሃሳብ የሚጋሩ በጅቡቲ የዶራሌ ኮንቴይነር ተርሚናል ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አብዲላሂ አድዋህ ሲጋድ በበኩላቸው፤ "በሎጅስቲክ ዘርፉ ትልቁ ችግር የመንገድ፣ የመሰረት ልማት እና የኮሪደር ነው" ብለዋል።

በአጠቃላይ ችግሩን በኢትዮጵያ ብሎም በጅቡቲ መንግሥት በኩል ለመፍታት ጥረቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

አሐዱ ከዚህ ቀደም በሰራቸው ዘገባዎች የአሸከርካሪዎች እንዲሁም የአሽከርካሪ ባለንብረቶች ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ