የካቲት 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ነባሩ ፓስፖርት የአገልግሎት ጊዜው እስኪያበቃና የዕድሳት ጊዜው እስኪደር ድረስ ጥቅም ላይ መዋሉን እንደሚቀጥል የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡

አገልግሎቱ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በኢትዮጵያ የተመረተውን አዲስ ኢ-ፓስፖርት፤ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በተገኙበት በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል፡፡

አዲሱን ፓስፖርት አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊ ዳዊት አሁን ላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ነባሩ ፓስፖርት የአገልግሎት ጊዜው እስኪያበቃ ጥቅም ላይ መዋሉን እንደሚቀጥል የገለጹ ሲሆን፤ የዕድሳት ጊዜው ሲደርስ በኢ-ፓስፖርት እንደሚተካ ተናግረዋል፡፡

Post image

ለዚህም ከአንድ ነጥብ 5 ሚልየን በላይ ኢ-ፓስፖርት ታትሞ መዘጋጀቱን በመግለጽ፤ 14 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት አገልግሎቱን ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁንም አስታውቀዋል፡፡

"አዲሱን ኢ-ፓስፖርት በሁለት ወር ከ10 ቀን ማግኘት ይቻላል" ያሉም ሲሆን፤ እስካሁን በነበረው ዋጋ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ከፓስፖርት በተጨማሪ "ከ10 በላይ የጉዞ ሰነዶችን እንዲዘምኑ ማድረግ ተችሏል" ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ተቋሙ ሪፎርም ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የጉዞ ሰነዶችን ዘመናዊ ለማድረግ እየሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

Post image

ከዚህ በፊት አገልግሎት እየተሰጠ የቆየው 20 ዓመት ባለፈው ቴክኖሎጂ መሆኑን የገለጹም ሲሆን፤ ይህንን ቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ መገንባት መቻሉ ትልቅ ድል ስለመሆኑ መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ለፓስፖርት እትመት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት የሚኖረው ፋይዳ ጉልህ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ አዲሱ ኢ-ፓስፖርት እስከአሁን ሀገሪቱ ካላት ፓስፖርት በአይነቱና በደረጃው እጅግ ከፍ ባለ ጥረት የተዘጋጀ የጉዞ ሰነድ መሆኑ ተመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ