የካቲት 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በተቋማት ላይ የሕጻናት የቀን ማቆያን ለማዘጋጀት የቦታ እና የዘርፉ ባለሙያዎች እጥረት ተግዳሮት እየሆነ እንደሚገኝ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

በሚኒስቴሩ የሕጻናት መብት ጥበቃ መሪ ሥራ አስፋጻሚ ወ/ሮ ዘቢደር ቦጋለ፤ በሕጻናት የቀን ማቆያ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን አሟልቶ ከመስራት አንጻር የሚነሱ ክፍተቶች መኖራቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በሚኒስቴር መስሪያ ቤት እና በተቋማት ደረጃ በየሦስት ወራት የሚለካበት አሰራር መኖሩን የገለጹት መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ፤ "የሕጻናት ማቆያን በሁሉም የግል እና የመንግሥት ተቋማት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የቦታ እጥረትና በዘርፉ የሠለጠነ እንዲሁም በበቂ ሁኔታ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች አለመኖር የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን የግል እንዲሁም የመንግሥት ተቋማት የሕጻናት የቀን ማቆያ የማዘጋጀት ኃላፊነትን ተቀብሎ ከመስራት አንጻር፤ በአሁኑ ወቅት መሻሻሎች እየተስተዋሉ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

አክለውም በዘርፉ መሻሻሎች ቢኖሩም በክልሎች ላይ አሁንም ክፍተቶች ስለመኖራቸው አንስተዋል፡፡

በክልሎች የመንግሥት እና የግልን ተቋማት ጨምሮ ከ250 በላይ የሓጻናት የቀን ማቆያ እንዲዘጋጅ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ወደ 6 ሺሕ የሚጠጉ ሕጻናት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም እንደ አጠቃላይ በክልሎች ላይ ያለው የህጻናት ማቆያ ትግበራ 'ሙሉ ለሙሉ የተሳካ ነው' ማለት እንደማይቻል ገልጸው፤ በሥራ ሂደቱ ላይ የሚነሱ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

መሪ ስራ አስፋጸሚዋ አክለውም በግል ተቋማት ላይ የሕጻናት የቀን ማቆያን በተመለከተ መረጃ የመሰብሰብ ሂደት ላይ ስለመሆናቸው የተናገሩ ሲሆን፤ መስፈርቱን ያሟሉ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/10 ተቋሞች ለወላጅ እናቶች የቀን ማቆያ እና የጡት ማጥቢያ ስፍራ እንዲመቻቹ ያዛል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ