ጥር 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የ52 ዓመቱ አሜሪካዊ ድሜትሪስ ፍሬዘር በአስገድዶ መድፈር እና ግድያ ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን ተከትሎ፤ በናይትሮጅን ጋዝ ታፍኖ ሕይወቱ እንዲያልፍ መደረጉ ተሰምቷል።
ድሜትሪስ ፍሬዘር በአላባማ በርሚንግሀም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ፓውሊን ብራውን የተባለች የሁለት ልጆች እናትን በመኖሪያ ቤቷ ገብቶ አስገድዶ ከደፈረ በኋላ የገደላት ሲሆን፤ እንዲሁም በሌላ ጊዜ የ14 ታዳጊ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል መፈጸሙ መረጋገጡን ተከትሎ በተደራራቢ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበት ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ተከሳሽ ድሚትሪስ ፍሮዘር በሞት ፍርድ እንዲቀጣ የተላለፈበት ሲሆን፤ የፍርድ ሂደቱ የተካሄደው የሞት ፍርድ የማይተላለፍበት ሚቺጋን ግዛት ውስጥ በመሆኑ ፍርዱ ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቀይሮለት እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
በአላባማ ወንጀል መፈጸሙ በፍርድ ቤት መረጋገጡን ተከትሎ ወደ አላባማ እስር ቤት ተላልፎ ሊሰጥ ችሏልም ተብሏል።
አላባማ ግዛት የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው ፍርደኞችን አየር አጥሯቸው እንዲሞቱ የሚያደርግ ሕግ ስላላት፤ ይህም ወንጀለኛ በናይትሮጅን ጋዝ ታፍኖ ህይወቱ እንዲያልፍ መደረጉ ተገልጿል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሳይቀር የሚቃወመው የናይትሮጅን ጋዝ ግድያ በአሜሪካዋ አላባማ ብቻ ይፈጸማል።
ይህን የግድያ አይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተቆርቋሪዎች "ጭካኔ የተሞላበት ነው" ሲሉ ይኮንኑታል።
የሞት ፍርድን የሚፈቅዱ ሌሎች የአሜሪካ ግዛቶችም ያሉ ሲሆን፤ የአላባማ ናይትሮጅን ጋዝ ግድያ አሁን ለሦስተኛ ጊዜ መፈጸሙን የአል አይን ዘገባ አመላክቷል።
አሜሪካ ካሏት 50 ግዛቶች ውስጥ 23ቱ የሞት ፍርድን መፈጸም የሚያስችል ሕግ ሲኖራቸው አቋርጠው የነበሩት አሪዞና፣ ኦሂዮ እና ተንሴ ግዛቶች ዳግም አስጀምረዋል።
ሀገሪቱ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ውስጥ ብቻ 25 ሰዎችን በሞት መቅጣቷም ተነግሯል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
አሜሪካ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ዜጋዋን በናይትሮጅን ጋዝ አፍና ገደለች
