ጥር 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በአፍሪካ አህጉር ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና ላይ አተኩሮ በጋና አክራ በተካሄደው የ"2025 የአፍሪካ ፕሮስፔሪቲ ዲያሎግ" ዓመታዊ የሽልማት መርሃ ግብር ላይ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት በማገናኘት ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየተጫወተ ላለው ሚና ላሳዩት የላቀ የአመራርነት ሚና የ “Leadership in Connecting Africa through Transport Award” ተሸላሚ መሆናቸው አየር መንገዱ አስታውቋል።

Post image


ይህ ሽልማት አፍሪካን እርስ በርስ በማገናኘት ቁርጠኛ የአመራርነት አስተዋፅዖ ላበረከቱ ግለሰቦች ዕውቅና የሚሰጥበት ሲሆን፤ የዘንድሮው የ “2025 የአፍሪካ ፕሮስፔሪቲ ዲያሎግ” የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የታላላቅ አህጉር ዓቀፍ የንግድ ተቋማት መሪዎች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በተገኙበት በጋና አክራ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይም አቶ መስፍን ጣሰው ለተሰጣቸው እውቅና ምስጋናቸውን ገልጸው፣ "ይህን ሽልማት በቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለራዕይ መሪዎች ሥም በማግኘቴ ትልቅ ክብር ተሰምቶኛል። የመላው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድን ታታሪነትና ትጋት ማሳያም ነው" ብለዋል፡፡

Post image

አክለውም "የእኛ ተልእኮ ሁሌም አፍሪካን ማስተሳሰር እና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ያለምንም ችግር የአየር ትራንስፖርት ማመቻቸት ነው። ይህ ሽልማት ግንኙነታችንን በማሳደግ እና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በመደገፍ ጥረታችንን እንድንቀጥል ያነሳሳናል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአህጉሪቱ በሚገኙ ከ65 በላይ መዳረሻዎች ኔትወርክን በማስፋፋት የበረራ አገልግሎቱን በማዘመን እና በዘመናዊ የካርጎ አገልግሎት ላይ ኢንቨስት ማድረጉን ከአየር መንገዱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ