የካቲት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አዋሽ ባንክ "ለላቀ የደንበኞች እርካታ እንተጋለን" በሚል መሪ ቃል ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የደንበኞች ሳምንት ከዛሬ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ አስጀምሯል።
በመርሃ ግብር ማስጀመሪያው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፀሀይ ሽፈራው፤ ባንኩ በአሁኑ ሰዓት ከ14 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ማፍራቱን ገልጸዋል።
አክለውም "ከምስረታው ጀምሮ የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካትና ደንበኞችን ማዕከል ያደረጉ ደንበኛ ተኮር አገልግሎቶችን እያቀረበ ሰላሳ ዓመታትን በስኬት መጓዝ ችሏል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ሣምንት የሚከበረው የደንበኞች ሳምንት ደንበኞችን ከባንኩ ጋር ስለነበራቸው አብሮነት ለማመስገን፣ ለማወደስና ለማክበር እንዲሁም በሠራተኞች ላይ የላቀ የደንበኞች እገልግሎት አሰጣጥ ለማንፈስን ለማስረጽ ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል።
በተጨማሪም ሁሉም የባንኩ የዋና መ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች በባንኩ ቅርንጫፎች በመገኘት በአካል ተገኝተው በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመለየትና ደንበኞችን ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ በመስጠት አገልጋይነትን ማስመስከር ታስቧል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በተለያየ ምክንያት ከባንኩ ጋር መስራት ያቆሙ ደንበኞች ጋር የነበረውን ግንኙነት ዳግም በማደስ የደንበኞችን እርካታ ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ የመርሃ ግብሩ ዋና ዋና ዓላማዎች መሆናቸው ተመላክቷል።
አዋሽ ባንክ በአሁኑ ሰዓት 273 ቢሊየን በላይ ተቀማጭ መሰብሰቡ የተገለጸ ሲሆን፤ ጠቅላላ ሀብቱም ከ397 ቢሊየን ብር በላይ መድረሱ ተነግሯል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ