የካቲት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በጋምቤላ ክልል፣ ኑዌር ብሔረሰብ ዞን አራት ወረዳዎች ላይ በተከሰተ አጣዳፊ ተቅማጥና የትውከት በሽታ ምክንያት፤ ሕጻናትን ጨምሮ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።

በሽታው በኑዌር ብሔረሰብ ዞን በአኮቦ፣ በዋንተዋ፣ ማኩዌይ እና ላሬ ወረዳዎች ላይ መከሰቱን ነው የክልሉ ጤና ቢሮ የገለጸው።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር አቤል አሰፋ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ከዚህ ቀደም በክልሉ አጎራባች ከሆነው አገር ደቡብ ሱዳን በሽታው ተከስቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ በአራቱ ወረዳዎች በሽታው መከሰቱን የገለጹ ሲሆን፤ በበሽታው ከተያዙት 136 ሰዎች መካከል ሕጻናትን ጨምሮ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ማለፋን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በበሽታው ከተያዙት ሰዎች ውስጥ 31 ሰዎች በሕክምና ላይ እንደሚገኙ በማንሳት፤ 96 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው ማገገማቸውን ገልጸዋል።

በሽታው በተከሰተባቸው አራት ወረዳዎች በጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሚመራ ቡድን በመላክ መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።

በሽታው ወደሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋም ሕብረተሰቡ አካባቢውን እንዲያጸዳና ንጽህናውን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

ለማንኛውም አገልግሎት የሚውልን ከቧንቧ፣ ከጉድጓድ፣ ከምንጭ፣ ከወንዝ እና ከመሳሰሉት የተቀዳ ውሃን በውሃ ማከሚያ መድኃኒቶች በማከም ወይም በማፍላት መጠቀም እንደሚገባም አስታውቀዋል።

ምግብን ከማዘጋጀት፣ ከማቅረብ እና ከመመገብ በፊት ከመጸዳጃ ቤት መልስ እና ሕጻናትን ካጸዳዱ በኋላ እጅን በሳሙና መታጠብ እንደሚገባም የቢሮው ኃላፊ አሳስበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ