የካቲት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 42ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡
አዋጁ በተቋሙ የተጀመረውን የሪፎርም ስርዓት ወደ ተግባር በመለወጥ በኢትዮጵያ የሕዝቡን የእርስ በእርስ መረዳዳት ባህል የማጎልበትና ተረጂነትን በዘላቂነት በሀገር አቅም መወጣትን ማዕከል በማድረግ የአደጋ ጉዳት ሰለባ ለሆኑ ዜጎች ከሰብአዊ ድጋፍ መርሆዎች፣ ከዘላቂ የልማት ፕሮግራሞችና ከሰላም መስፈን ጋር በማስተሳሰር ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ሞራላዊ ጉዳቱን ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል፡፡
ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በሦስት የተቋማት ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንቦች ላይ መሆኑ ተነግሯል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ ደንብ ዩኒቨርሲቲው አላማውን ለማሳካት የአደረጃጀት ማስተካከያዎችንና የአሠራር ለውጦችን ለማድረግ፤ የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ግሩፕ እና የመከላከያ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ማቋቋሚያ ደንብ ተቋሙ የሀገሪቱን የልዕለ ሕክምና፣ የዲያግኖስቲክ እና ተዛማጅ አገልግሎት ፍላጎትን ለማሟላት፤ እንዲሁም የተሻለ ህክምና ፍለጋ ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱ ታካሚዎች በሀገር ውስጥ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ለማድረግ እንዲሁም የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ማቋቋሚያ ደንብ የተቋሙን ተግባርና ኃላፊነት በመደንገግ ለሀገር እድገት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍ ሆኖ መቅረቡ ተገልጿል።
ምክር ቤቱም በቀረቡት ረቂቅ ደንቦች ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውሉ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሦስት የተቋማት ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቶ በሥራ ላይ እንዲውሉ ውሳኔ አሳለፈ
የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ተወስኗል
