የካቲት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከትላንት በስቲያ መካሄድ በጀመረው እና በትላትናው ዕለት በተጠናቀው 46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ የሕብረቱ የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ ተገልጿል።
"የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ በተከናወነው የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ከተያዙ አጀንዳዎች መካከል፤ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት የአምስት አባላት ምርጫ አንዱ ነበር።
በዚህም ኢትዮጵያ የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሆና የተመረጠች ሲሆን፤ ከፈረንጆቹ 2025 እስከ 2027 ድረስ ለሶስት ዓመታት የምክር ቤቱ አባል ሆና እንደምታገለግል ተገልጿል።
አሐዱም "ኢትዮጵያ በአፍሪካ የጸጥታው ምር ቤት አባል ሆና መመረጧን ተከትሎ፤ በቀጠናው እንዲሁም በአህጉር አቀፍ ደረጃ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ በምን መልኩ መጠቀም አለባት?" ሲል ዲፕሎማቶችንና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያዎችን ጠይቋል፡፡
በዚህም የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች አጥኚ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ማስሬ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሰላምና ፀታው ምክር ቤት አባል መሆኗ በቀጠናው ላይ ያላትን ተደማጭነት ለማሳካት በርካታ የውጭ ጫና ያለባት ሀገር ከመሆኗ አንፃርና በተለይም የባህር በር ለማግኘት የገባችበትን ጫና ለማቃለል የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
"አትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ሆና መመረጧ ተቋማዊ የሆነ አቅም ይፈጥርላታል" የሚሉት አቶ ደሳለኝ፤ "በተለይም ሰላም ማስከበር ላይ የነበራትን ልምድ የሚታወቅ በመሆኑ ይህ አባላነት ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያስገኝላት ነው" ብለዋል፡፡
"በመሆኑም ኢትዮጵያ ተቋማዊ የሆነ ቅርፅ ይዛ መንቀሳቀስ ስትጀምር አቅሟም ከፍ ይላል፤ ተሰሚነቷም እየጨመረ ይመጣል" ተናግረዋል፡፡
አቶ ደሳለኝ አክለውም፤ በአፍሪካ ሰላም ማስከበር ሂደት ውስጥም ትልቅ አቅም የሚፈጥርላት መሆኑንም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
"ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ እና ኬሎች የአህጉሩ ሀገራት ጋር በመሆን ትብብር በመፍጠር ሕብረቱ ላይ ያላትን ሚና ከፍ ማድረግ ያለባት ወቅት ላይ ትገኛለች" ሲሉ የሚገልጹት ደግሞ የቀድሞው ዲፕሎማት አምሳሳደር ጥሩነህ ዜናው ናቸው፡፡
ከመስራችነት ጀምሮ ያላትን ከፍተኛ ሚና በመጠቀም በተለይም እንድትዳከም የሚፈልጉ ሀገራት መኖራቸውን በመገንዘብ፤ ኢትዮጵያ በሕብረቱ ያላትን ሚና ከዚህ ቀደም ከነበረው በላቀ ደረጃ ከፍ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
አምባሳደር ጥሩነህ "ከተባባሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ጋርም በተያያዘ እንደ ሕብረት መስጠት አለበት እንጂ በሀገራት ደረጃ መሆን የለበትም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያም ከዚህ ቀደም በምጣኔ ሀብቱም ዘርፍ ጠንካራ ያልነበረች መሆኗን ያነሱት አምባሳደሩ አሁን ላይ ግን ከአምስት ጠንካራ ኢኮኖሚ በአፍሪካ አንዷ መሆኗን በማንሳት፤ "ጊዜው አሁን ሊሆን ስለሚችል አባልነት መጠየቅ ተገቢ ጉዳይ ነው" ሲሉም አሳስበዋል፡፡
"ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የምክር ቤቱ አባል ሆና መመረጧ ብሔራዊና ቀጣናዊ ፍላጎቶቿን እንዲሁም ጥቅሞቿን ከማስጠበቅ አንጻር ስልታዊ ጠቀሜታ ያስገኝላታል" ሲል፤ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ባጋራው መረጃ አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብርት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ ቀጠናዊ ፋይዳው የላቀ ነው ሲሉ ዲፕሎማቶች ገለጹ
