የካቲት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሩሲያ መንግሥት የመጀመሪያው የኒኩለር ቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ፤ ለመጪዎቹ 3 ዓመታት የሚያገለግል ሁለተኛው ፍኖተ ካርታ በትናንትናው ዕለት መፈረሙን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

Post image

የፍኖተ ካርታ ስምምነቱ የተደረገው ኢትዮጵያ እና ሩስያ በኢኮኖሚያዊ ትብብር፣ በባህል ልውውጥ፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና ሽግግር፣ በኢንቨስትመንት ፣ በትምህርት፣ በግብርና በንግድ ልውውጥ እና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ዘርፎች ላይ ይበልጥ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያለመ የምክክር መድረክ ላይ ነው።

የምክክር መድረኩ አላማ የኢትዮጵያና የሩስያ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ከመቼውም በላይ ከፍ በማድረግ የጋራ ስምምነቶችን መፍጠር መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የኢትዮ-ሩሲያ የበይነ-መንግሥታቱ የጋራ ኮሚቴ ጣምራ ሰብሳቢ የሆኑት ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከሩሲያ ፌዴሬሽን ጋር የምትጋራውን ለዘመናት ያስቆጠረ እና ታሪካዊ ግንኙነትን ከፍ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት እጅግ ፍሬማ ነው ብለዋል።

Post image

በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለው ወዳጅነት የዘመናት ግንኙነት ውጤት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የምናከናውናቸው የአጋር ስምምነቶች የዛሬውን አንገብጋቢ ጉዳዮች ከማንሳት ባለፈ ለቀጣይ ትውልዶች ጸንቶ የሚዘልቅና የሚለመልም አጋርነት መሰረት የሚጥል መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮ-ሩሲያ የበይነ-መንግሥታቱ የጋራ ኮሚቴ ጣምራ ሰብሳቢ የሆኑት የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ማክሲም ሬሼትኒኮቭ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት ሰፊ ሥራዎች እየሰራች ቢሆንም ግኑኝነቱን ይበልጥ በማጠናከርና በመቀራረብ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አንስተዋል።

Post image

በቀጣይ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በንግድ፣ በጤና፣ በባንክ ስርአት፣ በኢነርጂ፣ በቴክኖሎጂ፣ በማስ ሚዲያ፣ በቱሪዝምና ንግድ በሌሎችም ዘርፎች ለመስራት በጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚተጉ ገልጸዋል።

Post image

በምክክሩ ላይ የጤና ሚኒስቴር፣ የቱሪዝም ሚኒስትር፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን፣ የኢኒቨስትመንት ኮሚሽንና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማትና አመራሮች ተሳትፈውበታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ