የካቲት 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ዳግመኛ በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ምክንያት 40 ቀናት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ፤ 228 ሰዎች በበሽታው ተይዘው የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፋን የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
ወረርሽኙ በዋናነት በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ላይ የተከሰተ ቢሆንም፤ ግን አሁን ላይ ተስፋፍቶ ገንደውሀ ወረዳ፣ ጎንደር ከተማ እንዲሁም ባህርዳርን ጨምሮ ምዕራብ ጎጃም ቡሬ ከተማ እና አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ ላይ መከሰቱን በኢንስቲትዩቱ የበሽታዎችና የጤና ሁኔታዎች ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያ ሲስተር ሰፊ ደርብ ለአሐዱ ገልጸዋል።
ወረርሽኙ ታሕሳስ 24 ቀን 2017 ዓ.ም የተከሰተ መሆኑን በመጥቀስ ከታሕሳስ 24 እስከ የካቲት 3 ባሉ ጊዜያት ብቻ 228 የሚሆኑ ዜጎች በወረርሽኝ የተያዙ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ አራቱ ሕይወታቸው ማለፉን አስታውቀዋል።
ዘግይቶ ወደ ሕክምና ጣቢያ መሄድና ከነጭራሹም አለመሄድ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ምክንያት መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
ወረርሽኙ በክልሉ በሚገኙ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ተከስቶ እንደሆነ አሐዱ ላቀረበው ጥያቄ፤ የበሽታዎችና የጤና ሁኔታዎች ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያዋ በሰጡት ምላሽ፤ ታሕሳስ 24 እንደ አዲስ በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ምክንያት እስካሁን በመጠለያ ጣቢያዎች ላይ አለመከሰቱን ገልጸዋል፡፡
አክለውም፤ "ችግሩ እንዳይከሰት ግን የቅኝት ሥራ እና የጤና ባለሙያዎችን በመመደብ መሰረታዊ የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል" ብለዋል።
የመድኃኒት አቅርቦት ከዓለም የጤና ድርጅትና ሌሎች ድርጅቶች እንዲሁም፤ ከክልሉ ጤና ቢሮና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተገኙ ግብአቶች ወረርሽኙ ወደተከሰተባቸው ቦታዎች መላኩንም ጨምረው ገልጸዋል።
በመሆኑም ማህበረሰቡ በተለይም ብዙ ሕዝብ በሚገኝበት ቦታዎች ላይ ወረርሽኙን እንዲጠነቀቅ ያሳሰቡት ባለሙያዋ፤ እንደ ማሕበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተለይም ወረርሽኙ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ የጤና ትምህርት እና የብክለት መከላከል ተግባራት እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ከቀናት በፊት የአውሮፓ ሲቪል ጥበቃ እና የሰብአዊ እርዳታ ኦፕሬሽንስ (ECHO) በክልሉ ዳግመኛ በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ምክንያት፤ 160 ሰዎች ተይዘው የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን መግለጹ ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በአማራ ክልል 40 ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ በኮሌራ ወረርሽኝ 228 ሰዎች ሲያዙ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ
