ታሕሳስ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትላንትናው ዕለት ለሊት 9 ሰዓት ከ52 ላይ እስከ ዛሬ ሲከሰት ከነበረው በመጠኑ ከፍ ያለና 5 ነጥብ 8 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ በአፋር ክልል አምቦሳ አካባቢ መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂ ሰርቬይ መረጃ አመላክቷል።

የመሬት መንቀጥቀጡ ንዝረት በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በተደጋጋሚ በስፋት ሲሰማ እንደነበርም አሐዱ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ከሚገኙ ነዋሪዎች ማረጋገጥ ችሏል።

ይህም የመሬት መንቀጥቀጥ ሰሞኑን እየተከሰቱ ካሉ ርዕደ መሬቶች በመጠኑ ከፍተኛው ሲሆን፤ ረዘም ላሉ ሰከንዶች መቆየቱም ተነግሯል።

Post image

የመሬት መንቀጥቀጠለ የተከሰተው በአፋር ክልል ከአቦምሳ ከተማ 56 ኪሎ ሜትር ርቀት እንዲሁም ከአዳማ ከተማ 137 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ መሆኑን ተመላክቷል።

በተጨማሪም ትናንት ምሽት 2:01 ሰዓት ላይ በፈንታሌ ዙሪያ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 3 እንዲሁም፤ ቀን 11:27 ሰዓት ላይ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 2 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱም ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በአፋር ክልል፣ ዱለሳ ወረዳ በተከሰት የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በበርካታ ሥፍራዎች ላይ ፍል ውሃዎች እየተፈጠሩ ይገኛሉ።

Post image

በመሬት መንቀጥቀጡ ሳቢያ በፈንታሌ እና በዶፈን ተራራ መካከል የተፈጠረው የመሬት ስንጥቅ ክፍተቱ እየጨመረ መሆኑንም የተገለጸ ሲሆን፤ በተራራው ላይ ጭስ እየወጣበት የነበረው ቦታ በአሁን ወቅት እሳት እየወጣበት እንደሚገኝ በአካባቢው ያሉ ምንጮች ጠቁመዋል።

የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል ከፍ ማለት ትርጉሙ ምንድነው? በሚለው ጉዳይ ላይ ከአሶሽየትድ ፕረስ እና ከሌሎች ምንጮች የተገኙ መረጃዎች ይህን ያመላክታሉ።

ቁጥሮቹ ሲተነተኑ (በሬክተር ስኬል):-

👉 ከ4 ነጥብ 0 በታች፤ አነስተኛ ነው፤ ትንሽ ብቻ ነው የሚሰማው። አልፎ አልፎ ጉዳት ያስከትላል።

👉 ከ4 ነጥብ 0 እስከ 4 ነጥብ 9 ድረስ፤ ጉዳቱ አብዛኛውን ጊዜ አነስተኛ ነው።

👉 ከ5 ነጥብ 0 እስከ 5 ነጥብ 9 ድረስ፤ መጠነኛ ነው። በደንብ ባልተገነቡ ሕንፃዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።

👉 ከ6 ነጥብ 0 እስከ 6 ነጥብ 9 ድረስ፤ ጠንከር ይላል። ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች በተለይም አሮጌ ወይም በደንብ ባልተገነቡ ህንፃዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።

👉 ከ7 ነጥብ 0 እስከ 7 ነጥብ 9 ድረስ፤ መሠረተ ልማት እና ሕንፃዎች ሊያፈርስ ይችላል።

👉 እንዲሁም 8 ነጥብ 0 እና ከዚያ በላይ ሲሆን ደግሞ፤ ብዙ ጊዜ አስከፊ ጉዳት ማለትም የሰው ሕይወት መጥፋት እና ውድመት ሊያስከትል ይችላል። በተለይም በተከሰተበት አካባቢ ከባድ ጉዳት ያስከትላል።

Post image

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተደጋጋሚ እየተከሰተ የሚገኘው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በተለይም የክስተቱ መነሻ በሆኑ አካባቢዎች ላይ በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ስጋትን የደቀነ ሲሆን፤ በአካባቢዎቹ የሚገኙ ነዋሪዎችን ወደሌላ ስፍራዎች የማዘዋወር ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ እየተገለጸ ይገኛል።