የካቲት 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ረቡዕ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 2:00 ላይ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ-ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ሥሙ "ሞቢል" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፤ በእንጨትና በብረታ ብረት ውጤቶች ማምረቻና ማኅበር ላይ በአጋጠመ የእሳት አደጋ ከፍተኛ የንብረት ወድመት ማጋጠሙን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር 6 ሰዓት እንደፈጀ የተገለጸ ሲሆን፤ እሳቱን ለማጥፋት ጥረት ሲያደርጉ ከነበሩ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች መካከል 5 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ላይ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል።
በእሳት አደጋው የእንጨትና የብረታ ብረት ውጤቶች እንዲሁም በተወሰኑ ማሽነሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለአሐዱ ገልጸዋል።
የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር የኮሚሽኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች፣ የጸጥታ አካላት፣ የደንብ ማስከበርና የአካባቢው ማኅበረሰብ ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብና ቅንጅት እሳቱ በአቅራቢያው ወዳሉ ሌሎች ማምረቻና ተቋማት ተዛምቶ የከፋ ውድመት ሳያስከትል ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ተችሏል ተብሏል።
ፖሊስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ባለማድረግ ለእሳት አደጋው መንስዔ ምክንያት ናቸው ብሎ የጠረጠራቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር አውሎ እያጣራ እንደሚገኝም የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አስታውቀዋል።
አደጋ የደረሰበት ቦታ በክፍለ-ከተማዉ ለእሳት አደጋ ተጋላጭ ተብለው ከተለዩ የሥራ ቦታዎች ውስጥ አንዱ መሆኑም ተመላክቷል።
በመሆኑም በማምረቻና በንግድ ስፍራዎች አካባቢ በጥንቃቄ ጉድለትና ቸልተኝነት ምክንያት የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ለመከላከል ለጥንቃቄ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ኮሚሽን መ/ቤቱ አሳስቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ኮልፌ ቀራንዮ አካባቢ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለማጥፋት በተሰማሩ 5 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ
