የካቲት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል የነበረውን ግጭት ያስቆመውን የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሂደት በተመለከተና ከስምምነቱ "ሌሎች ምን እንማር?" በሚል ርዕስ ትናንት የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም በአፍሪካ ሕብረት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
በሪፖርቱ ላይም ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተከናወነው የሰላም ስምምነት ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለው እሳቤ በተግባር የተረጋገጠበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህ ውይይት ላይም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እና የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረሚካኤል(ዶ/ር) የተገኙ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ እድሪስ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ሕብረትን ላለፉት ስምንት ዓመታት በሊቀ መንበርነት የመሩት ተሰናባቹ ሙሳ ፋኪ ማኅማት፣ የቀድሞ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪ ቡድን አባል ኡሊሲንጎን ኦባሳንጆ እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ ኮሚሽነሮች ተገኝተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን በመክፈቻ ንግግራቸው የደቡብ አፍሪካ፣ የኬንያ እና የናይጄሪያ መንግሥታት እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ሂደቱን በመደገፍ ለተጫወቱት የላቀ ሚና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በአንፃራዊነት ሰፊ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ጌዲዮን፤ የሁለቱም ወገኖች ዘላቂ ትሩፋት የሂደቱን አካባቢያዊ ባለቤትነት ማረጋገጥ እንዲሁም በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ያለው የማያሻማ ቁርጠኝነት የማያጠያይቅ መሆኑንም ለተሳታፊዎች ተናግረዋል።
የፌደራል መንግሥት ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተፈፃሚ እንዲሆን እና በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ከፍተኛ ሃብት በማሰማራት ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ እና የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሊሲንጎን ኦባሳንጆ በበኩላቸው፤ ሁለቱም ወገኖች አስተዋይ አመራር እና ለሰላም ሂደቱ ልዩ ቁርጠኝነት ማሳየታቸው ትልቅ ምዕራፍ ነው ተብሎ እንደሚታሰብ ተናግረዋል።

አፍሪካውያን የስምምነት ሂደቱ ባለቤት መሆናቸው አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት አህጉር እንድትሆን የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ የሚያሳይ ነው ያሉት ኦባሳንጆ፤ ለሌሎች በግጭት ውስጥ ለሚገኙ ሀገራትም ተሞክሮዎችን ይሰጣል ብለዋል።
በዚሁ የግምገማ መድረክ ላይ ከአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር የሆኑት አምባሳደር ባንኮሌ አዲኦዬ ከሰላም ሂደቱ የተገኙ 11 ቁልፍ ትምህርቶች ላይ አጭር ገለጻ አድርገዋል።

ስምምነቱ የትጥቅ ውጊያን በማጥፋት፣ በፓርቲዎች መካከል ያለውን ግንኙነት በማሻሻልና የሰላም ስምምነቶችን ተግባራዊነትና ዘላቂነት በማሳየት ሰላምና መረጋጋትን ወደ ነበረበት ለመመለስ ወሳኝ መሳሪያ መሆኑን አስምረውበታል።
ከአንድ ሰአት በላይ የዘለቀ ውይይት ከተካሄደ በኋላ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

በምላሻቸውም "የዛሬው መድረክ እስካሁን የሄድንበት ርቀት መገምገም ነው። ከጀመርነው ፍጥነት አንፃር ገና ያላለቁ ነገሮች አሉ። ግን በተሻለ ፍጥነት መጨረስ የምንችልበት እድል ለማግኘት ነው የመጣነው" ብለዋል።
አክለውም "ሰላምን ከመስበክ፣ ሰላምን ከመተግበርም ሆነ ከምንም ነገር በላይ ግን ተፈናቃዮች ወደወትሮ ሕይወታቸው የሚመለሱበትና ሕገ-መንግስቱ በሚያስቀምጠው መሰረት የፕሪቶሪያ ውል ሙሉ ለሙሉ ተፈፃሚ የሚሆንበት ጉዳይ ላይ ነው ሀሳብ የተለዋወጥነው። በቀጣይም በዚህ መሰረት የምንቀጥል ይመስለኛል" ሲሉ ተናግረዋል።
ተሰናባቹ የአፍሪካ ሕብረት ኮምሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት በበኩላቸው፤ የሰሜኑን ጦርነት ለመፍታት የተደረገው የሰላም ንግግር በኢትዮጵያ ትልቅ ውጤት ያመጣ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

አጀንዳ 2063 እ.ኤ.አ በ2030 የጥይት ድምጽ የማይሰማባትን አፍሪካ እውን ማድረግ አንዱ ግቡ ቢሆንም፤ ይህን እቅድ ለማሳካት አገራቱ ብዙ ርቀት አልሔዱበትም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትልቅ ትምህርት ሊወሰድበት እንደሚገባም ሙሳ ፋቂ አጽዕኖት ሰጥተዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ