የካቲት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ፖለቲካም ሆነ በትግራይ ፖለቲካ ታሪክ በጉልህ የሚጠራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ በትናንትናው ዕለት 50 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

አሐዱም ይህንን ቀን ምክንያት በማድረግ ያነጋራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የካቲት 11 በወቅቱ የነበረን ጭቆና ለማስቆም፣ በቋንቋ የመናገርን መብት ለማስከበር እና ሁሉም ሕዝብ እኩልነትን ለማስከበር የተደረገ ትግል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ "ቀኑን ማክበር ተገቢ ጉዳይ ቢሆንም፤ ህወሓት ከትጥቅ ትግል በኃላ በተለይም ወደ ስልጣን ከወጣ በኃላ የተቋቋመበትን ዓላማ የረሳ ፓርቲ ነው" ሲሉ የፓርቲ አመራሮች ተናግረዋል፡፡

የውድብ ናፅናት ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የግዚያዊ አስተዳዳር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዶክተር ደጀን መዘገብ ከአሐዱ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ "የካቲት 11 የትግራይ ሕዝብ የራስ ዕድል በራስ የመወሰን ያደረገው የ100 ዓመታት ትግል ነው" ሲሉ ገልጸውታል፡፡

በ1967 የካቲት 11 ይህ ትግል በተደራጀ መንገድ በመምጣት ያለፉትን ትውልድ ያነሳውን ጥያቄ ወደ ጫፍ ለማምጣት የተደረገ ትግል ነው ብለዋል፡፡

"ይሁን እንጂ እንደ ሀገር ይህ ቀን የፌደራል ስርዓትን መስርቶልናል" ያሉት ዶክተር ደጀን፤ "እንደ ትግራይ ግን ብዙ ዕድሎችን ቀምቶናል" ብለዋል፡፡

ሌላው ሀሳባቸውን ለአሐዱ የሰጡት የሳልሳይ ወያኔ ትግራይ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብርሃነ አፅብሃ በበኩላቸው የካቲት 11 መከበር ያለበት በዓል ነው ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩ ሲሆን፤ "ይሁን እንጂ ቀኑ ለትግራይ የጠቀመው ነገር የለም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከ2010 ወዲህ መንግሥት ከተለወጠ በኃላ በተለይ በኢህአዴግ መካካል የተፈጠረው ልዩነት እና እሱን ተከትሎ የመጣው ጦርነትም በክልሉ የነበረው የተጠራቀመ ጭቆና መኖሩ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ህወሓት አውራ ፓርቲ ሆኖ የዘለቀ ፓርቲ ቢሆንም፤ ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ የበደለ ፓርቲ ነው" ሲሉም የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የካቲት 11 የሕዝብ በዓል ነው የሚል አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ያደረገበት አካሄድ ተገቢ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

"ህወሓት ሲፈልግ የፓርቲ ሲፈልግ ሕዝብ በዓል ያደርጋል" ያሉም ሲሆን፤ "መንግሥታዊ በዓል ሆኖ ቢቀጥል ችግር የለውም ይሁን እንጂ ህወሓትና ሕዝብን መለየት ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የየካቲት 11 በዓል ምክንያት በማድረግ በትግረኛ ባሰተላለፉት መልዕክት "ለመላው የትግራይ ሕዝብ እንኳን አደረሳችሁ" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም "ባለፉት ቅርብ ዓመታት ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የተከተልነው የግጭት መንገድ የካቲት 11 ዓላማን የሳተ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ከባድ ዋጋ ተከፍሎ ወደ ውይይት የመጣን ቢሆንም አሁንም ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በጠመንጃ የመፍታት ፍላጎት እየታየ ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት የተከበረው የካቲት 11 በዓልም በህወሓት ለሁለት መከፈል የተነሳ የተደረጉ እርቆችም ፍሬ ማፍራት ባለመቻላቸው፤ በጋራ ለማክበር የታሰበው ውጥን ሳይሳካ መቅረቱን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ