ታሕሳስ 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማሕበራት ምክር ቤት ከምርጫው በኋላ በተነደፉ አዳዲስ አሰራሮች ላይ ለውጥ ለማምጣት እየሰራ እንደሚገኝ በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ ላይ አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም በርካታ የመመሪያ ክፍተቶች እንደነበሩበት የገለጸው ም/ቤቱ፤ የግዥና ንብረት አስተዳደር፣ የሰው ሀብት ልማት መመሪያ፣ የፋይናንስ መመሪያ ክፍተቶች እንደነበሩበት ተናግራል።

በመጪው ወር የሚያሂደው የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ አዲስ አበባን የሚወክሉ የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮችን ምርጫ እንደሚያደርግም የምክር ቤቱ የቦርድ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሽንቁጤ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ አሳታፊ የሚሆንና ቁመናውን ለማደራጀት እንዲሁም፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ ነጋዴዎችን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን በመግለጫው ተናግሯል።

ንግድ ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ጠቅላላ ጉባኤ በተመለከተና የገንዘብ አስተዳደር ጋር በተያያዘ ከአመራሮቹ ጋር የንትርክ ሁኔታ ላይ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ስለዚህም ይህንን ችግር ለማጥራትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን በማድረግ አዳዲስ አመራሮችን ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ከ482 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች እንደሚገኙና ዓመታዊ የአባላት ግዴታውን በክፍያ የሚወጣ አባል ከ4 ሺሕ አንድ መቶ እንደማይበልጥ የተናገሩት ፕሬዝዳንቷ፤ ምክር ቤቱ የአባላቱ ቁጥር ለማሳደግ ውጥን ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ የቦርድ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሽንቁጤ፤ "ምክር ቤቱ የኮሪደር ልማት ፈረሳው በአዲስ አበባ በሚገኙ ነጋዴዎች ላይ ያሳደረው አሉታዊ ጫና ምንድን ነው?" የሚል ጥያቄም ከጋዜጠኞች ቀርቦላቸ የነበረ ሲሆን መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል።