ጥር 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ የተሰነዘሩ የኦዲት ግኝቶች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎችን በዛሬው ዕለት ገምግሟል።
በዋና ኦዲተር ተለይተው በቀረቡ የኦዲት ግኝቶች ላይ ቋሚ ኮሚቴው፤ የመሬት እና የኃይል አቅርቦት፣ የፈቃድ መስጠት፣ ማደስ እና መሰረዝ፣ ከቀረጥ ነጻ የገቡ ቁሳቁች ፈቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር፣ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የሚገኙበት ደረጃ እና አፈጻጸም፣ የመረጃ ፍሰት እና መሰል ጉዳዮች ላይ የነበሩ የኦዲት ግኝቶች ላይ ያተኮሩ 9 ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡
በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምላሽ እንዲሰጥባቸው ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የውጭ ሀገር ዜጎች የሥራ ቅጥርን የተመለከተው ይገኝበታል፡፡
በአንድ ተቋም የሚያገለግሉ የውጭ ሀገር ዜጎች ከፍተኛ አመራሮችን ሳይጨምር ከአጠቃላይ ሠራተኛው ከ10 በመቶ እንዳይበልጡ የሚያስገድድ ሕግ ቢኖርም፤ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ አለመኖሩን ያነሱት በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሕግ እና ፖሊሲ አማካሪ ሐብታሙ ስማቸው ናቸው፡፡
የሕግና ፖሊሲ አማካሪው አቶ ሐብታሙ፤ "በኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኩል የተዘጋጀው መመሪያ የውጭ ሀገር ዜጎች በሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ላይ ሲቀጠሩ የተቀጣሪዎቹ ሙያ እና ክህሎት ያለው ሰው ሀገር ውስጥ መኖር አለመኖሩን የማረጋገጥ ሥራውን አስቸጋሪ አድርጎታል" ብለዋል፡፡
"ኮሚሽኑ ከቅጥር በተጨማሪ በእድሳት ወቅትም የውጭ ሀገር ዜጎች የዕውቀት ሽግግር ስለማድረጋቸው የሚቆጣጠርበት አሰራር በአዲሱ መመሪያ ተካቷል" ያሉ ሲሆን፤ የክህሎት ደረጃ ለመስጠትም አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኦዲት ግኝቶች ላይ ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ በኦዲት ግኝቶች ላይ የተወሰደው የእርምት ማስተካከያ ዝቅተኛ በመሆኑ ተቋሙ ማስተካከያ የተደረገባቸውን እና ሳይስተካከሉ የቀሩ ግኝቶችን በድርጊት መርሃ ግብር በግልጽ ለይቶ እስከ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያቀርብ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የውጭ ሀገር ዜጎችን የሥራ ቅጥር የሚወስን ዝርዝር መመሪያ መዘጋጀቱ ተገለጸ
