ጥር 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤዉን ከጥር 24 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፤ ወደ ጉባኤዉ ስፍራ ለመግባት በፀጥታ ሃይሎች ታግዶ እንደነበር አስታውቋል።
ፓርቲው እሁድ ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ አብርሃም ጌጡ ፓርቲውን እንዲመሩ መምረጡ ይታወሳል።
በዚሁ 10ኛው ጠቅላላ ጉባኤው ላይ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ማሻሻያ ማድረጉንም አስታውቋል።
አሐዱ ያነጋገራቸው የፖርቲው አዲስ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት አቶ አብርሀም ጌጡ፤ ጥር 24 ቀን 2017 ወደ ጉባኤ ቦታ ለመግባት በፀጥታ ሃይሎች በመከልከላቸው ተቸግረው እንደነበር ገልጸዋል።
በተለይም የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ በዕለቱ ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም በተመሳሳይ ሰዓት የብልፅግና ፖርቲ ጠቅላላ ጉባኤ የሚካሄድበት ዕለት በመሆኑ፤ በፀጥታ ምክንያት ወደ አዳራሹ መግባት ክልከላ እንደተደረገባቸው ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ ፓርቲው ባለፈው 34 ዓመታት በተለይም ፓርቲውን በመሩት አራት አመራሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ሲደርስባቸው እንደነበር ከአሐዱ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
የፓርቲው ፈተና ዘርፈ ብዙ መሆኑን የገለጹም ሲሆን፤ በተለይም ምርጫ በደረሰ ቁጥር የአባላት እስር የአመራሮች መንገላታት እና ሌሎች ከፍተኛ የሆኑ ፈተናዎችን አልፎ 10ኛ ጉባኤው ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ 'ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ አለባችሁ' ብሎ ትዕዛዝ በሰጠዉ መሰረትና ጉባኤውን ለማድረግ በተወሰነለት ቀን ለማድረግ ዝግጅት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ በነበረበት ወቅት ወደ መሰብሰቢያ አዳራሽ እንዳይገባ ተከልክሎ እንደነበርም አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ የነበረውን እንግልት ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በማሳወቅ ጉባኤ ማድረግ እንዳለበት ተማምኖ 10ኛ ጉባኤውን ማከናወን መቻሉንም ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 1162/2011 የምርጫ ምዘገባና ሥነ-ምግባር አዋጅ መሰረት ፓርቲዎች በየሦስት ዓመቱ ጉባኤ ማድረግ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ