የካቲት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የጣሪያና ግድግዳ ግብር መክፈያ ቀነ ገደብ በመጪው የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ገልጿል።

በገቢዎች ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት አቶ ኃላፊ ሰውነት አየለ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ከ400 ሺሕ በላይ ዜጎች የጣሪያና ግድግዳ ግብር መክፈል አለባቸው በሚል ተለይተዋል።

ነገር ግን እስካሁን ባለው ሂደት 228 ሺሕ 222 ግብር ከፋዮች የቤትና ቦታ ግብር መፈጸማቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ይህም የዕቅዱ 51 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አክለውም የቤትና ቦታ ግብራቸውን ከከፈሉ ግብር ከፋዮች 2 ነጥብ 24 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ የቤትና ቦታ ግብር የሚከፍሉ ግብር ከፋዮች ግብሩ ያለቅጣትና ወለድ የሚከፈልበት ጊዜ እየተጠናቀቀ መሆኑን ያስታወቁም ሲሆን፤ ከየካቲት 30 ቀን 2017ዓ.ም በኃላ ለመክፈል የሚመጡ ሰዎች በቅጣትና ወለድ ክፍያ እንደሚስተናገዱ ጨምረው ገልጸዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በሚነሱ ያልተጣሩ መረጃዎች ከመክፈል ወደ ኃላ ያሉ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ቀኑ ሲደርስ ከሚፈጠር ወከባ ለመዳን ባለው ጊዜ ውስጥ ክፍያቸውን እንዲያጠናቅቁ ጠይቀዋል።

ስለሆነም የጣሪያና ግድግዳ ግብር ያልከፈሉ ዜጎች ከተቀመጠው ቀን በፊት ግብራቸውን እንዲከፍሉ ሲሉ፤ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ሰውነት አየለ አሳስበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ