ጥር 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ጎንደር ዩኒቨርስቲ ለአካል ጉዳተኞች ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በተለይም ከሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመወዳደር ከአሸነፈው የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ፕሮጀክት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት፤ በርካታ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ወጪያቸው ተሸፍኖ ትምርህታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተመላክቷል።

በአሁኑ ወቅትም በአጠቃላይ ከ600 በላይ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እንዳሉ በዩኒቨርስቲው የሕግ መምህርና በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ፕሮጀክት የዩኒቨርስቲ ሠራተኞች አቅም ግንባታና ከትምህርት ተመላሾች አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር በቀለ አዳነ ለአሐዱ ተናግረዋል።

"ፕሮጀክቱ ከኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተጨማሪም ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የመጡ ተማሪዎች በድህረ ምረቃ ተመልምለው እንዲማሩ የሚፈቅድ በመሆኑ፤ በርካታ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው ትምርህታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ" ብለዋል።

በዚህ ዓመት ብቻ ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሌላድ የተመለመሉ ከ30 በላይ ተማሪዎች ትምርህታቸውን በዩኒቨርሲቲው እየተከታተሉ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው፤ "ከዚህ ባለፈ በራሱ በጀት የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል" ብለዋል።