ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በእስር ላይ የሚገኙ የፓርቲው አባል በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና በአባሎች ላይ የሚደረገው ማስፈራራት፣ አፈና እና እስር በአስቸኳይ ይቁም ሲል ጠይቋል
"ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊ ችግሮች ተውጠው በመኖርና ባለመኖር የሚገኙ ከመሆናቸውም በላይ እንደ አገር የመዝለቋ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና አጠያያቂ ከሆነ ውሎ አድሯል" ሲልም ነው ፓርቲው የገለጸው።
ኢሕአፓ ይህን ያለው በወታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መገለጫ ሲሆን፤ በመግለጫውም የሐረሪ ክልል የፓርቲው አባልና የክልሉ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራር አባል የሆኑት ተስፋሁን ምልኬ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቋል።
በተጨማሪም "በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን በደል በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ድምፅን ለማሰማት የማይቻልባት፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የዜጎችን ጥቅም እንዲያስከብሩ መጠየቅ ወንጀል የሆነባት አገር ሆናለች" ብሏል።
"ለሕዝብ ድምፅ በመሆን የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላትን ማስፈራራት፣ ማፈንና ማሰር የተለመዱ እኩይ መንግሥታዊ ተግባራት ከሆኑ ውለው አድረዋል" ሲልም ተችቷል።
የፓርቲው አባል ተስፋዬ ምልኬ ቅዳሜ ታሕሳስ 26 2017 ዓ.ም ከመኖሪያ ቤታቸው ተወስደው መታሰራቸውን የገለጸው ፓርቲው፤ "በሕገ መንግሥት አንቀጽ 19 ተራ ቁጥር 3 በግልጽ ያስቀመጠውን “የተያዙ ሰዎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው የሚለው ሕግ ተጥሷል" ሲል ከሷል።
'ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት' በሚል ወንጀል መያዛቸውን የገለጸም ሲሆን፤ ከታሰሩ ከሁለት ቀናት በኃላ ፖሊስ ጣቢያ አውጥተው ወዴት እንደወሰዷቸው አለመታወቁንና ዘመዶቻቸው፣ ጓደኞቻቸውና እንዲሁም የድርጅቱ አባላት ለማፈላለግ ሙከራ ቢያደርጉም ሊያገኙቸው አለመቻላቸውን አስታውቋል።
"የመንግሥት አካላት ሕግን እያከበሩ ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ፓርቲያቸው ዜጎችን በብረት መዳፍ ውስጥ አስገብቶ፣ ረግጦና ጨፍልቆ ለመግዛት እንዲችል መሣሪያ መሆናቸው እጅግ አሳፋሪ ድርጊት ነው" ያለው ፓርቲው፤ ድርጊቱ "ኢ-ሰብዓዊ ነው" ሲል አውግዟል።
ፓርቲው ከዚህ ቀደም በአፋር ክልል የአመራር አባል የሆኑትን አቶ ጀማል እንዲሁም የቤኒሻንጉል ክልል የአመራር አባል የሆኑትን አቶ ማንደፍሮ ቆለጭም ለእሥራት ተዳርገው እንደነበረ አስታውሷል።
ስለሆነም ተስፋሁን ምልኬ በአስቸኳይ እንዲፈቱና በአባሎቻቸው ላይ የሚደረገው ማስፈራራት፣ ማፈንና፣ ማሠር በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ሲል አጽንዖት ሰጥቷል።