ጥር 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት እና የፍልሰት መረጃን በሚያመነጩ አስራ አንድ የመንግሥት ተቋማት መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት የፍልሰተኞችን መረጃ ለማጋራት የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።

የመግባቢያ ስምምነቱን ከፈረሙ ተቋማት መካከል የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ ይገኙበታል።

ስምምነቱ በሀገሪቱ ያልተደራጁና ተደራሽ ያልሆኑ እንዲሁም ያልተናበቡና የትንተና ሥራ ያልተከናወነባቸውን መረጃዎች ዘመኑ በሚፈልገው ልክ በማደራጀት ለሚፈለገው ዓላማ ጥቅም ላይ እንዲውል ይረዳል ተብሏል።

በተጨማሪም የፍልሰት መረጃን በአግባቡ ለመሰብሰብ የሚያስችል በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራርን የሚፈጥር መሆኑ ተጠቅሷል።

ለዚህ የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ የሚውል የፍይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ጽ/ቤት በኩል መደረጉም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በታሕሳስ 2023 በ2ኛው የስደተኞች መድረክ ከገባቸው ስድስት ቃል-ኪዳኖች መካከል፤ የስደተኞች መረጃን በብሔራዊ ስታትስቲክስ ሥርዓት ውስጥ እንዲካተት ማስቻል አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዚህም መሰረት የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ለመግባቢያ ስምምነቱና ገቢራዊነት ልዩ ትኩረት በመስጠት አቅም በፈቀደ የገንዘብ፣ የቴክኒክና ቁሳዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተመላክቷል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ