ጥር 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኤች አይቪ ኤድስ ሥርጭትን ለመቀነስ ጊዜው የሚዋጀውን ቴክኖሎጂ በማስተዋወቅ ለሕዝብ ግንዛቤ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ አብነት አሰፋ ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገው ድጋፍ በአንፃሩ ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ስርጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመሆኑ አንጻር፤ የዓለም ሀገራት ድጋፍ እንደ ከዚህ ቀደሙ አለመሆኑን ገልጸዋል።
አሐዱ "የበሽታው ሥርጭት እንዳይባባስ ምን ምን የሥራ ክንውኖች እየተሰሩ ነው?" ሲል ኃላፊዋን የጠየቀ ሲሆን፤ በምላሻቸውም "የወረርሽኙ ስርጭት አሁንም ትኩረት የሚሻ ነው" ብለዋል።
ለቫይረሱ ወጣቶች የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን ያነሱት ኃላፊዋ፤ ይህን ለመቀነስ በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች ቦታዎች እየተሰራ ቢሆንም ስርጭቱን ለመቀነስ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረት ተግዳሮት መሆኑን አንስተዋል።
አክለውም "የተለያዩ የሞባይል መተግበሪያዎችን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው" ብለዋል።
በኢትዮጵያ እስካሁን ከ605 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
በተጨማሪም በዓመቱ 7 ሺሕ 428 ሰዎች በኤች አይቪ እንደሚያዙ መረጃው ያመላከተ ሲሆን፤ ወደ 10 ሺሕ 65 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ምክንያት እንደሚሞቱ እ.አ.አ የ2024 አገራዊ የኤች አይ ቪ ስርጭት ግምት አመላክቷል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ