የነዳጅ እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ንድግ ቢሮ ሥር እንዲተዳደር ከተደረገ በኋላ በአንጻራዊነት የተረጋጋ መሆኑን የገለጸው ቢሮው፤ ማደያዎች ነዳጅን በመደበቅ እንደሌላቸው የሚያስመስሉበትን አሰራር ማስቀረት መቻሉን ተናግሯል፡፡

የንግድ ቢሮው የገበያ መረጃ ጥናት እና ማስተዋወቅ ዳይሬክተር አቶ ሙሰማ ጀማል ለአሐዱ በሰጡት ቃል፤ 'የማሽን ብልሽት አጋጠመ'፣ 'ነዳጅ አለቀ' እና ሌሎችንም ምክንያቶች የሚያቀርቡ ማደያዎች በባለሙያዎች ፍተሻ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በዚህም አሰራሩ ከተጀመረ ባለፉት 39 ቀናት ውስጥ 6 ማደያዎች ሕገ ወጥ ተግባር ፈፅመዉ መቀጣታቸውን እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍል ከተማ የሚገኙ ሁለት ማደያዎች ነዳጅ የሚያቀርብላቸው ተቋም ጋር ያላቸው ውል በመቋረጡ ሥራ ማቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡

"እርምጃ የተወሰደባቸው ስድስት ማደያዎች ነዳጅ እያለ 'የለም' በማለታቸው፤ የማስጠንቀቂያ እና በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል" ሲሉ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

Post image

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የነዳጅ ማደያዎች ዕለታዊ የነዳጅ አቅርቦት መጠንን ጥቅምት ወር ላይ ይፋ ማድረግ መጀመሩ ይታወቃል፡፡

ለአብነትም የዛሬ ሕዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም ጠዋት ማደያዎች ሥራ ሲጀምሩ የነበራቸው የነዳጅ መጠን ሲታይ፤ ቤንዚን 3 ሚሊየን 167 ሺሕ 210 ሊትር፤ ናፍጣ ደግሞ 3 ሚሊየን 820 ሺሕ 464 ሊትር እንደነበር መረጃው ያሳያል፡፡

በተያያዘ ዜና በትናንትናው ዕለት በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስምንተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፤ በአዲስ አበባ አንድ ቀን በተደረገ አሰሳ ከ120 ማደያዎች ስድስቱ ብቻ አገልግሎት ሲሰጡ መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

አክለውም በነዳጅ የአቅርቦት እና የስርጭት ችግር መኖሩን ገልጸው፤ ይህን ችግርን ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

68 የሚሆኑ ነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ እያላቸው 'የለም' ሲሉ መገኘታቸውንም ያብራሩት ሚኒስትሩ፤ ከ105 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች ላይ በመላው ሀገሪቱ እርምጃ መወሰዱንና ከዚህ ወስጥ ከአንድ ሺሕ በላይ የሚሆኑት በእስራት አንዲቀጡ መደረጉን አስታውቀዋል።