አሐዱም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ "የነበረውን ችግር መፍትሄ መስጠት አልተቻለም ወይ?" ሲል የጋሞ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮን ጠይቋል።

የቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ጩባ በሰጡት ምላሽ፤ በፓርኩ ድምበር ጥሰው ከገቡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በመወያየትና ሌሎች ቦታዎችን በማመቻቸት እንዲወጡ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር በጋራ መሠራቱን ገልጸዋል።

አክለውም በባሕላዊ መንገድ የዱር እንስሳትን በሚያድኑ ግለሰቦች ላይ አስተማሪ እርምጃዎችን በመውሰድ የታየውን ችግር መቅረፍ መቻሉን አስረድተዋል።

ሆኖም ግን አሁንም የተወሰኑ ችግሮች እንዳሉ አብራርተው፤ "ፓርኩ በፀጥታ ምክንያት ዝግ ነው ተብሎ በማሕበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጨው መረጃም ሀሰተኛ ነው" ሲሉ የቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ጩባ ለአሐዱ ተናግረዋል።

ኃላፊው አክለውም አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ በመሆኑ ሊጎበኙ የሚችሉ ቦታዎችን የማስፋፋት ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ወደ ፓርኩ በሚኬድበት ወቅት አልፎ አልፎ የሚከሰት የፀጥታ ችግር መኖሩን ያልደበቁት አቶ ገዛኸኝ፤ "አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡

Post image

በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ከሚገኘው 52 ነጥብ 2 ሜዳማ የግጦሽ መሬት ውስጥ 51 በመቶውን ማለትም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በፓርኩ ውስጥ ነዋሪ በሆኑ የምዕራብ ጉጂ ገላና ወረዳ ኤርጌንሳ ቀበሌ አርብቶ አደሮች፤ በመቶ ሺሕ በሚቆጠሩ ከብቶቻቸው በመጋጡ በፓርኩ ያሉ የዱር እንሰሳት ህልውና አደጋ ውስጥ መውደቁ ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡