የመጀመሪያ ዙር የገቡትን የቀድሞ ተዋጊዎችን በጥሩ አቀባበል ወደ ካምፕ ገብተዉ የሚገባውን ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ለአሐዱ የተናገሩት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ተስፋዓለም ይህደጎ ናቸው፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም ወደ መቐለና ዕዳጋ ሀሙስ ማዕከላት ከገቡት 2 ሺሕ ገደማ ሰልጣኞች ውስጥ፤ 1 ሺሕ 640 የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች ስልጠናውን አጠናቀው ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀሪዎቹም በተመሳሳይ ስልጠና ወስደዉ የወጡ ሲሆን፤ "በአጠቃላይ ከ2 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ ተሰርቷል" ብለዋል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ የቀድሞ ተዋጊዎችን ለማቋቋም የሚሰጠው ገንዘብ አነስተኛ መሆኑ ይነሳል፡፡ ይህንን በሚመለከት አሐዱ የጠየቃቸው የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ተስፋዓለም ይህደጎ፤ "ገንዘቡ አንሷል መባሉ ተገቢ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታና አቅም በላይ መሆኑን በመግለጽ፤ የቀድሞ ተዋጊዎች ችግሮቻቸውን ሊፈታ የሚችል በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥር ያለ አብይ ኮሚቴ መቋቋሙን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ኮሚቴው የሙያ ክህሎት ግብዓቶች ከተገኙ የማስተባበር ሥራ የሚሰራ መሆኑ የተነሳ ሲሆን፤ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በመቅረፅ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ሥራዎችን እየሰሩ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በአሁን ወቅት በሥሩ ከ300 ሺሕ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን መዝግቦ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው በትግራይ ክልል የሚገኝ ነው፡፡