ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ያሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በተመለከተ መረጃ የሚናገሩ ተቋማት መበራከታቸውን ገልጾ፤ የሚያወጡት ጥናት ዙርያ ተአማኒነት እንደሚጎድላቸው አስታውቋል።

"በአብዛኛው የሚወጡ መረጃዎች ወደ አንድን ወገን ያጋደሉ ናቸው" ያለም ሲሆን፤ በዚህ ላይ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስቧል።

እየቀረቡ ያሉ አሃዛዊ መረጃዎች 'ጥናት' በሚል ሰበብ የሚቀርቡ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ "በተለይም ከፋይናንስ ደህንነት አንፃር የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ክትትል ሊያደርግበት ይገባል" ብሏል።

"በየመጠለያ ጣቢያው የሚገኙትን ተፈናቃዮችን 'እንደግፋለን' 'እርዳታ እናደርሳለን' በሚል፤ ለራሳቸው ጥቅም የሚያውሉ በረጂ ድርጅትት ሥም የተቋቋሙ አካላት መኖራቸውን ደርሼበታለሁ" ሲልም ለአሐዱ አስታውቋል።

የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች በተመለከተ በኮሚሽኑ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ለአሐዱ የገለጹት የኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አለማየሁ ወጫቶ (ዶ/ር)፤ ባለፈው ሩብ ዓመትም የተመዘገቡ ውጤቶች አመርቂ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በጎ ፍቃደኛ ረጂዎችና አጥኚዎችም የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በተመለከተ የሚፈልጉት መረጃ ካለም ከኮሚሽኑ የመረጃ ቋት እንዲጠቀሙ እናበረታታለን" ሲሉም ዶክተር አለማየሁ አክለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከረጂ ተቋማት ገንዘብ ለማግኘት ሲባል፤ የተጋነነ ቁጥር እንዳለ የማስመሰልና የማቅረብ አዝማሚያ እየተስተዋለ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ተግባር እውነተኛ ረጂዎችን የሚያወዛግብ ከመሆኑ በተጨማሪም፤ የኮሚሽኑ መልካም ሥም የሚያጠለሽና በተቋሙ አመለካከት እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከየአካባቢያቸው የተፈናቀሉ በሚልየኖች የሚቆጠሩ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራውን ሲገለጽ ቢቆይም፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ ኮሚሽኑ ገልጿል።

የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይህንን ይበል እንጂ፤ ተፈናቃዮች አሁን ላይ አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ፤ አሐዱ በተለያዩ ጊዜያቶች ያሰባሰባቸው መረጃዎች ይጠቁማል።